የጋና የዴሞክራሲ ሽግግር አብነት ፤ የእኛ ጉድለት ምንድን ነው? | ዳዊት ዋበላ
ሐሳብ

የጋና የዴሞክራሲ ሽግግር አብነት ፤ የእኛ ጉድለት ምንድን ነው? | ዳዊት ዋበላ

አንዲት አገር ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን የሚያስፈልጋት ምንድን ነው? ዴሞክራሲያዊ አገር ለመሆን ምን ምን ሁኔታዎች (requisites) ያስፈልጋሉ? ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለማድረግ በሚደረግ ሒደት (democratization) ውስጥ ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎች/ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ወዘተ… የሚሉት ጥያቄዎች የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራንን ሲያከራክሩ የኖሩ፣ አሁንም የሚከራክሩ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የዘመናዊነት ንድፈ-ሐሳብ (modernization theory) አቀንቃኝ የሆኑ የፖለቲካል ሳይንስና የሶሲዮሎጂ ምሁራን አንዲት አገር ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን ካስፈለገ መጀመሪያ የዳበረ ኢኮኖሚ እና/ወይም ጠንካራ መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ (middle class) ያስፈልጋታል ይላሉ፡፡ ባረንተን ሙር የተባለው ምሁር፡- “በበኩሉ ቡርዧ ከሌለ ዴሞክራሲ የለም” (no bourgeois no democracy) ሲል “The social origins of democracy and dictatorship” በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፉ ያትታል፡፡ በጥቅሉ ሁሉም አገሮች ከዝቅተኛ ኢኮኖሚ ወደ ከፍተኛና ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደሚሻጋገሩ፣ በዚህ ሒደትም በጊዜ ሒደት የዝመና አንዱ አካል የሆነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን እንደሚሆን ብዙ ተጽፏል፡፡

ይህን ንድፈ-ሐሳብ በጽኑ የሚኮንኑ ሌሎች ምሁራን በበኩላቸው ዴሞክራሲና ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚያገናኛቸው ነገር የለም ባይባልም አንዱ ለሌላው መፈጠር የግድ ሆኖ መቅረብ ግን የለበትም፡፡ የዳበረ ኢኮኖሚ ሳይኖራቸው የሚደነቅ የዴሞክራሲ ሥርዓት የገነቡት እነ ሕንድ ያሉትን ያህል የዳበረ ኢኮኖሚ ኖሯቸው ኢዴሞክራሲያዊ የሆኑ እንደ ሩሲያ፣ ቻይና ወዘተ… ያሉ አገሮች መኖራቸውን በመጥቀስ ጠንካራ መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡

ዴሞክራሲን ከባህል ጋር የሚያያይዙትም አሉ፡፡ ባህልን እንደ ዋና መስፈርት ወይም ቅድመ-ሁኔታ የሚያስቀምጡ ምሁራን በአንዲት አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን ካስፈለገ ለዴሞክራሲ መብቀልና መፋፋት ምቹ የሆነ ባህል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ እነዚህ በአመዛኙ ከሶሲዮሎጂና ማኅበራዊ ሥነ-ልቡና መስኮች አካባቢ የሚመጡ ምሁራን ከግለሰቦች፣ ቤተሰቦች እና ከማኅበረሰቡ አኗኗር ጋር አያይዘው፣ ዴሞክራሲን ሊሸከም የሚችል ባህል ያለውን ያህል ለኢዴሞክራሲ ምቹ የሆነ ባህልም መኖሩን ይገልጻሉ፡፡ “ሕዝቡ ስለዴሞክራሲ ያለው እይታ ምንድን ነው? ከዴሞክራሲ ውጪ ያሉ አማራጮችን እንዴት ያያቸዋል? ዴሞክራሲ የከተማው/የአገሩ ብቸኛው አጀንዳ ነውን?” ወዘተ… እያሉ ይጠይቃሉ፤ ያጠናሉ፡፡

ሌሎችም በርካታ ክርክሮች እና ንድፈ-ሐሳቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የዘውግና የሃይማኖት ልዩነቶችና ስንጥቆች (cleavages) ለዴሞክራሲ እንቅፋት ናቸው አይደሉም የሚል ሰፊ ክርክርም አለ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን ሊሆን የሚችለው በልኂቃኑ መሀከል መተማመንና መግባባት ሲኖር ነው የሚሉ ምሁራንም አሉ፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ጠንካራና ደካማ ጎን አላቸው፡፡

ኢትዮጵያና ጋና

በቅርቡ ለሥራ ጉዳይ ወደጋና (አክራ) አቅንቼ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በአክራ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመት ያህል ስለቆየሁ የጋናን የፖለቲካ ሁኔታ በተወሰነ ደረጃም አውቀዋለሁ፡፡ በጋና የዴሞክራሲ ሽግግር ላይ የተጻፉ መጻሕፍትንም አነባለሁ፡፡ ይህች አጭር ጽሑፍ በቅርቡ ወደ አክራ አቅንቼ ከጋና ጋዜጠኞች ጋር ባሳለፍኳቸው 6 የውይይት ቀናት ላይ የተመሠረተች ናት፡፡

ኢትዮጵያ የሺሕ ዘመናት የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ሲኖራት፣ ጋና እንደ አገር (የተለያዩ በብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ግዛቶች ወደ አንድ መጥተው “ጋና” በሚል ስም) እ.ኤ.አ. በ1957 ነጻነቷን ያወጀች አገር ናት፡፡ የታወቁት ምሁርና የነጻነት ታጋይ ኩዋሜ ንኩርማ የመጀመሪያው የዚያች አገር ርእሰ ብሔር ሲሆኑ፣ በመፈንቅለ መንግሥት ተወግደው አገሪቱ በወታደራዊ አስተዳደር ስር ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡

ጋና የረዥም ጊዜ የአገረ መንግሥትነት ታሪክ የላትም፡፡ በዚህ ምክንያት ጋናዊያን በክፉውም በደጉም የሚጋሩት የጋራ ታሪክ እና በዚህ የታሪክ ጉዞ ያዳበሩት የጋራ ብሔራዊ ዕሴት/ዕሴቶች በበቂ ሁኔታ የላቸውም፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ በሚያስደንቅ ሁኔታ የረዥም ጊዜ ታሪክ አለን ከምንለው፣ የውጭ ጠላቶቻችን ለመመከት በጋራ ተነስተን በጋራ ከተዋደቅነው፣ ተጋድሎ ዘመኖቻችን ሁሉ በአንድ ጉድጓድ ከተቀበርነው ከእኛ ከኢትዮጵያዊያን የተሻለ የጋራ ብሔራዊ ዕሴት እና ማንነት (national identity) ይስተዋልባቸዋል፤ አዳብረዋል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

“ረዥም የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ትልቅ ጥቅም ያለውን ያህል በሚገባ ካልተያዘ ዕዳም ሊሆን ይችላል፡፡ ግሪክን፣ ቱርክን፣ ታላቋ ብሪታኒያን፣ ስፔንን ወዘተ… ተመልከት፡፡ ገናና የሆነ የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ያላቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ያስገበሩና ቅኝ የገዙ አገሮች ናቸው፡፡ ግን ታሪካቸው ዕዳ ሲሆንም ይታያል፡፡ የኢትዮጵያም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ በአገራችሁ ታሪክ ነው ትልቁ የፖለቲካ አውድማ የሆነው፡፡ የአገራችሁ የፖለቲካ ልኂቃን የአሁኑንና ወደፊቱን አገሪቱን ሁኔታ ከመቅረጽ ይልቅ ታሪክ ላይ ተቸንክረው ቀርተዋል” ይላል ጋዜጠኛ በፈር አንኮማህ፡፡

እውነትም አንዳንድ ምሁራን “የታሪክ ሸክም” (The burden of history) የሚሉት ነገር ሰለባዎች ሆነናል ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በውድም ይሁን በግድ አገረ መንግሥት ሆናለች፡፡ ይህ ደግሞ ሌሎች፣ በተለይም ብዙዎቹ የአውሮፓ አገሮች የሚጋሩት የአገረ መንግሥት የምሥረታ ሒደት ነው፡፡ ይህች አገር ከነችግሯም ቢሆን ከራሷ አልፋ የሌሎች ጥቁር ሕዝቦችም መኩሪያ የሆኑ ታሪኮችን የሠራች አገር ናት፡፡ አሁን የጎደላት ጠንካራ ኢኮኖሚ እና እኩልነትና ፍትሐዊነት የነገሠበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ የዛሬውና ወደፊቱ የዚህች አገር አጀንዳዎች መሆን ያለባቸው እነዚህ ጉዳዮች ናቸው፡- የኢኮኖሚ ልማት፣ እኩልነት፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ፡፡

ጋና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከኢዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተሸጋግራለች፡፡ ያች አገር ይህን ሽግግር ያደረገችው የዘመናዊነት ንድፈ-ሐሳብ አቀንቃኞች እንደሚሉት ጠንካራ ኢኮኖሚ ስላላት አይደለም፡፡ ጋና ዛሬም ቢሆን ድሃ አገር ናት፡፡ በዚህ ረገድ ከኢዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ለማድረግ የዳበረ ኢኮኖሚ መገንባት ወይም ብሔራዊ ከበርቴ ማፍራት የግድ እንዳልሆነ ወይም እንደ ቅድመ-ሁኔታ እንደማይቀመጥ ከጋና ሁኔታ ማየት ይቻላል፡፡

ጋና ዴሞክራሲያዊት አገር የሆነችው ለዴሞክራሲ የሚመች ነባር ባህል ስለነበራትም አልነበረም፡፡ ይህን የሚያሳይ ታሪክም ሁኔታም የለም፡፡ አፍሪካ-ተኮር (Afro-centric) የሆኑ ሰዎች የአፍሪካ ነገዶች ከዴሞክራሲ ጋር የሚቀራረብ አስተዳደራዊ ሥርዓት እንደነበራቸውና እንዳላቸው ሊነግሩን ቢፈልጉም፣ እንደ እውነቱ ከሆነ በአፍሪካ ውስጥ ዴሞክራሲ ኖሮ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ጋና ዴሞክራሲያዊት አገር የሆነችው የቀደመ ለዴሞክራሲ ማበብ ምቹ የሆነ ባህል/ዕሴት ስላላት ነው የሚለው ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ የጋና ጓደኞቼ እንደሚገልጹት እንደሚያውም የባህል ጉዳይ ከተነሳ ጋና ለዴሞክራሲ የማያግዝ፣ ከፍተኛ ክፍፍልና አለመተማመን የነበረበት ባህል ነበር የነበራት፡፡

አንጃ ኦሴ (Anja Osie) የተባሉ ምሁር “Elites and Democracy in Ghana: A Social Network Approach” በሚለው ጽሑፋቸው በሚገባ እንደገለጹትና የጋና ጓዶቼ እንደሚያረጋግጡት ለጋና ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገር ዓይነተኛ ሚና የተጫወቱት የዚያች አገር ልኂቃን ናቸው፡፡

ጋና ከቅኝ ግዛት ወደ ነጻነት፣ ከዚያም ወደ መፈንቅለ መንግሥትና አምባገነናዊ አገዛዝ ከተሸጋገረች በኋላ በሥልጣን ላይ ባሉትና ሥልጣን ባልያዙት የጋና ልኂቃን፣ በፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ በሲቪክ ማኅበራት መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሙያ ማኅበራት ወዘተ… የጋራ ጥረትና መግባባት ነው ወደ ዴሞክራሲ የተሸጋገረችው፡፡ ጋና ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት የአገሪቱ ልኂቃን ናቸው፡፡

በዚህ የጋና ልኂቃን ልባምና አርቆ አስተዋይ ጥረት አገሪቱ ዛሬ የምታስቀና አገር ሆናለች፡፡ ዴሞክራሲ ጊዜ ይፈጃል፣ አሜሪካ የዳበረ ዴሞክራሲን ለመገንባት ሁለት መቶ ዓመት ፈጅቶባታል፣ እኛ ከፀረ ዴሞክራሲ የተላቀቅነው ገና በቅርቡ ስለሆነ እንዲህ በአጭር ጊዜ ዴሞክራሲን ለመገንባት አይቻልም ወዘተ… እየተባለ በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ሲነገረን ከርሟል፡፡ ከአሜሪካና አውሮፓ የሚመጡ “አማካሪዎችም” እንደተለመደው በመናቅ መንፈስ ቀስ ብለን ልንደርስ እንደምንችል ሲነግሩን ቆይተዋል፡፡

የነ ጋና የሽግግር ታሪክ ግን ይህን አይነግረንም፡፡ በጣም በርካታ ብሔረሰቦች ያሏት አገር፣ እዚህ ግባ የማይባል የኢኮኖሚ ልማት ያላት አገር፣ ረዥም የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ያልነበራት፤ ይልቁንም በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ የነበሩ አራት ግዛቶች ተደምረው የፈጠሯት አገር አብነት ሊሆን የሚችል ሥርዓት ገንብታለች፡፡ የጋና ልኂቃን ምስጋና ይግባቸው!

የየካቲት 66 አብዮት ሲፈነዳ እነ ፖርቹጋል፣ እነ ስፔንና ግሪክ ገና ከአምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ለመውጣት ደፋ ቀና እያሉ ነበር፡፡ ግን ያ ኢዴሞክራሲያዊ የሆነ ታሪካቸው ዴሞክራሲያዊ አገሮች እንዳይሆኑ አላገዳቸውም፡፡ ሕንድም፣ ናይጀሪያም ከእኛ በእጅጉ የሚበልጡ ብሔረሰቦችን ያቀፉ አገሮች ናቸው፡፡ ግን ዴሞክራሲን ከመገንባት ያገዳቸው ነገር የለም፡፡ ሶማሊያ አንድ ብሔርና አንድ ሃይማኖት ብቻ የነበራት አገር ናት፡፡ ግን እንኳን ዴሞክራሲን ልትገነባ ህልውናዋም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን የልኂቃን ሚና ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልኂቃን እስካሁን ተፈትነው ወድቀዋል፡፡ አሁን በያዝነው መንገድ ከቀጠልን መጪው ዘመንም የከፋ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

December 3, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *