ሕዝበኝነት ከተቋማትና ሥርዓታት (institutions) ይልቅ ‹የሕዝቡ አስተሳሰብና ዕውቀት› ይበልጣል የሚል መንፈስ አለው፡፡ ከልኂቃኑ ይልቅ ሕዝቡ፣ ከተቋማትና ሥርዓታት ይልቅ የሕዝቡ የራሱ የአኗኗርና አሠራር ዘይቤ ዓይነተኛ (authentic) እና ወሳኝ ነው ብሎ የማመን ዝንባሌ አለው ሕዝብኝነት፡፡ በጥቅሉ ሕዝበኝነት ከርዕዮተ ዓለም፣ ከተቋማዊ አሠራር እና ከሥርዓታት ጋር በተቃርኖ የቆመ ነገር ነው፡፡
ሕዝበኞች በተለያየ መልክ የሚገለጹ ቢሆንም ሕዝብን የሚያማልሉ ኮርኳሪ ቃላትን በመጠቀም የብዙሃኑን ሕዝብ ቀልብ ለመሳብ በሚያደርጉት ጥረት ይመሳሰላሉ፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅመው በጥናትና ምርምር የተገኘ ነገር ምንድን ነው ሳይሆን፣ ሕዝቡ የሚፈልገው ምንድን ነው? ከሚል መነሻ በመነሳት ስሜት ቅስቃሽ ኮርኳሪና ንግግሮችን በማድረግ የሕዝብን ቀልብ ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ትልቁ የአገር ነቀርሳ ነው፡፡
በዓለም ላይ በጣም ብዙ ሕዝበኛ መሪዎች ታይተዋል፡፡ ኮርኳሪ ቃላትን በመጠቀም የሕዝቡን ስሜት እየቆሰቁሱ ለሥልጣን የበቁ፣ ከዚያ በኋላ ግን ሥልጣን ላይ ያወጣቸውን ሕዝብ መልሰው ያስለቀሱ ገዥዎች ነበሩ፤ አሉም፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን እነ ሻለቃ መንግሥቱ ኀይለ ማርያምን “መንጌ”፣ “ቆራጡ አብዮታዊ መሪ”፣ “የሕዝብ ልጅ” ወዘተ… እየተበሉ፤ እነሱም በፊናቸው “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!” እያሉ እየተናገሩ፣ አስፈላጊ ሲሆንም በሠራዊቱ እና በሕዝቡ መካከል እየተገኙ አብረው እየበሉና እየጠጡ፣ በአደባባይ እንባ እያፈሰሱ እንዴት በሕዝቡ ልብ ውስጥ እንደገቡ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ለኮ/ል መንግሥቱ አምባገነነን መሆን የሕዝቡ ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ አብረዋቸው የነበሩት ጓዶቻቸው (እና በኋላ አገልጋዮቻቸው) ሚናም እጅግ ትልቅ ነበር፡፡
ኢትዮጵያዊያን አምባገነንን የመኮትኮት ክፉ ባህል አለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በአንድ ቡድን ወይም በአንድ ግለሰብ ዙሪያ የመኮልኮል እና የማደግደግ ባህል የዴሞክራሲ ፀር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ለግለሰብ የማደግደግ ክፉ ልክፍት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጊዜም ታይቷል፡፡ የፓርቲ እና የመንግሥት አመራሮች ከላይ እስከታች የአቶ መለስ አምላኪዎች ነበሩ፡፡ እንደ አቶ መለስ መናገር የተለመደ ባህል ነበር፡፡ አቶ መለስ በዘመናት ውስጥ ከሚፈጠሩ ባለ ራዕዮች አንዱ ናቸው እየተባለ ያልተነገረ ነገር አልነበረም፡፡
“ዐቢይ ይምራን”!
አሁንም እዚያው ነን፡፡ አሁንም ከተለመደው ለግለሰብ የማደግደግ ባህል አልተፈወስንም፡፡ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጪ ያለው አማራጭ የፀረ ዴሞክራሲና የብተና አማራጭ ነው ሲሉን የከረሙት ጎበዞች ዓይናቸውን በጨው አጥበው ከብልጽግና ፓርቲ ውጪ ያሉት ፓርቲዎች አማራጭ የላቸውም፤ ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ያላት ብቸኛ አማራጭ ብልጽግና ሲሆን፣ መሪዋም ዐቢይ አሕመድ ብቻ ናቸው እየተባለ ነው፡፡ “ዐቢይ ይምራን” እየተባለ በየቦታው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶግራፍ እየተለጠፈ ነው፡፡ ትናንትና የአቶ መለስን ፎቶግራፍ ሲሳለሙ የነበሩ ካድሬዎች ዛሬ ተመልሰው የዶ/ር ዐቢይን ፎቶግራፍ በስልክ ስክሪናቸው ላይ ሳይቀር አስቀምጠውታል፡፡
ኢትዮጵያ የምትከተለው የፓርላሜንታዊ ሥርዓት መሆኑ እየታወቀ፣ ኢትዮጵያዊያን የምንመርጠው ፓርቲን እንጅ ግለሰብን አለመሆኑ እየታወቀ ልክ ፕሬዚዳንት የምንመርጥ ይመስል “ዐቢይ ይምራን” መባሉ ምን ያህል ረዥም ርቀት ሄደን ግለሰቦችን እንደምናመልክ፣ ምን ያህል የግለሰብ ተክለሰብዕናን በመገንባት ልክፍት እንደተለከፍን ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከዚህ አደገኛ የዘመናት ልክፍት ካልተፈወስን በስተቀር በየጊዜው የግለሰቦች ባሪያ ከመሆን አንድንም፡፡ ከዚህ አደገኛ ልክፍት ካልተፈወስን በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደናፈቀን ይቀራል፡፡ ዴሞክራሲን መገንባት የሚችሉት በፖለቲከኞች ላይ ልጓም ማበጀት የሚችሉ ቁርጠኛ ሕዝቦች ብቻ ናቸው፡፡
Leave a Reply