ኢትዮጵያ እና የቦትስዋና ፈለግ | በሪሁን አዳነ
ሐሳብ

ኢትዮጵያ እና የቦትስዋና ፈለግ | በሪሁን አዳነ

ሻሹር ጉፕታ ስለ ቦትስዋና ተናግሮ አይጠግብም፡፡ አገሩ ደቡብ አፍሪካ “የቦትስዋና ፈለግ” ብሎ የሚጠራውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንድትከተል አጥብቆ የሚከራከረው ጉፕታ፣ ቦትስዋና ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች እየተገኘ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡ በርእሰ-ጉዳዩ ላይ መጽሐፍም እያዘጋጀ ነው፡፡ ግን ለምን ቦትስዋና? የቦትስዋና ፈለግስ እንደምን ያለ ነው?

የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (SADC) መቀመጫ የሆነቸው ቦትስዋና በአህጉራችን ከሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ ዲሞክራሲያዊ አገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1966 ከብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች ወዲህ [በቅርቡ ወደ ሥልጣን የመጡትን ጨምሮ] አምስት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዚዳንቶችን አይታለች፡፡ ቦትስዋና አነስተኛ የቆዳ ስፋት ያላት፣ ወደብ አልባ የሆነችና እዚህ ግባ የሚባል ወታደራዊ አቅም የሌላት አገር ብትሆንም፣ በቀጠናዊና ዓለም ዐቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የምታራምደው አቋምና የምታሳርፈው ተጽዕኖ ከብዙዎቹ ትልልቅ የሚባሉ የአፍሪካ አገሮች በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ የአገሪቱ “ገር ኀይል” (soft-power) ከውስጣዊ ሰላሟና ከገነባችው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይመነጫል፡፡ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ መርሆዎች መከባበርና ዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብቶች መከበርና የሕግ የበላይነት፣ እንዲሁም ቀጠናዊና ዓለም ዐቀፋዊ ሰላም ሲሆኑ፣ ያዳበረችው የዲሞክራሲ ዕሴትና የገነባችው ኢኮኖሚ በቀጠናው የምትጫወተውን ሚና ከፍ አድርጎላታል፡፡

እነዚህን መርሆዎች መሠረት በማድረግ የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያካሂዱ፣ የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያ መብቶች እንዲያክሩ እና ለሕግ የበላይነት እንዲገዙ ግፊት ታደርጋለች፡፡ የአካባቢው አገሮች ኢዲሞክራሲያዊ እርምጃዎችን ሲወስዱና የዜጎቻቸውን ሰብአዊ መብቶች ሲጥሱ የቦትስዋና መሪዎች እርምጃውን በድፍረት በአደባባይ በመተቸትና በማውገዝ ይታወቃሉ፡፡ የቦትስዋና መሪዎች አካሄድ እንደ ሮበርት ሙጋቤ ላሉ የአካባቢው ፈለጫ ቆራጭ መሪዎች የማይመች ቢሆንም ዲሞክራሲ በቀጠናው ስር እንዲሰድ ግን ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ነው፡፡

ጉፕታ “የቦትስዋና ፈለግ” የሚለው ይህንን የደቡብ አፍሪካዊቷን አገር የውጭ ግንኙነት ዘይቤ ነው፡፡ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እና ይህን ውስጣዊ አቅም ተጠቅሞ በቀጠናው አገሮች ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳረፍ፡፡

“ድንበር አያስፈልግም”

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ፣ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መሀከል ሰላምና ትብብር ሊኖር እንደሚገባ ብቻ ሳይሆን፣ የቀጠናው አገሮች በመሀከላቸው ያለውን ድንበር አስወግደው በሒደት ሊዋሐዱ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደምም እንደ ተስፋ ጽዮን መድኀኔና ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ ያሉ ምሁራን የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በኮንፌደሬሽን ወይም በፌደሬሽን መልክ ስለሚተሳሰሩበት መንገድ አበክረው ሲናገሩና ሲጽፉ ቆይተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተያየት እንደማይስማሙ የሚገልጹት ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ በበኩላቸው፣ “በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መሀከል ድንበር አያስፈልግም የሚለው ሐሳባዊነት (idealism) የሚጫነው አስተያየት ነው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መነሻ በጎ ቢሆንም አስተያየታቸውና ፍላጎታቸው ከነባራዊው የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ በእጅጉ የራቀ ነው፤” በማለት ይከራከራሉ፡፡ “እንዲያውም፣ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መሀከል ሰላም እንዲሰፍን ካስፈለገ፣ ሊወሰድ የሚገባው ተቀዳሚ እርምጃ ተጎራባች አገሮች የሚቀበሉትና የሚያከብሩት ድንበር እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ እንኳን ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት በሌላቸው የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ይቅርና በአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች መሀከልም ጠንካራ ድንበር አለ፡፡ ስለሆነም የድንበር አጥር አያስፈልገንም፣ መዋሐድ አለብን ወዘተ. እየተባለ የሚቀርበው አስተያየት የቀጠናውንም ሆነ የዓለምን ሁኔታ ያላገናዘበ ሐሳባዊነት የሚጫነው አስተያየት በመሆኑ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ቀማሪዎች በደንብ ሊፈትሹት ይገባል፤” ይላሉ ዶ//ር ብርሃኑ፡፡

ድንበር አያስፈልግም ከመባሉና የቀጠናው አገሮች በኮንፌደሬሽን ወይም በፌደሬሽን መልክ ይተሳሰሩ የሚል አስተያየት ከመቅረቡ በፊት ሊከወኑ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት አሉ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ እያንዳንዱ የአፍሪካ ቀንድ አገር ዘመናዊ አገረ-መንግሥት (modern state) እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ይጠበቅበታል፡፡ ጉራማይሌ የሆነ የአገረ-መንግሥት ቁመና ባላቸው አገሮች መሀከል የሚደረግ ኅብረት ከንቱ ነው፤ የጋራ ዲሞክራሲያዊ ዕሴት በሌላቸው አገሮች መሀከል የሚደረግ ትስስርም የእምቧይ ካብ ነው፡፡

ለመተባበር መከባበር

በአፈና ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ አገሮች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚቀመረው በመስኩ የትምህርት ዝግጅትና ተሞክሮ ባላቸው ባለሙያዎች ሳይሆን በገዥዎች በመሆኑ፣ ተቋማዊ ባሕርይ የለውም፤ በግለሰቦች ስሜና ይሁንታ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መሀከል ትልቅ እንቅፋት ፈጥረው ከቆዩት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ ቀጠናው ከትናንት እስከዛሬ የፈላጭ ቆራጮች መፈንጫ በመሆኑ የአገሮች ግንኙነትም ከመሪዎች ስሜትና ፍላጎት ጋር የሚለዋወጥ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የየአገራቱ መሪዎችና ገዥ ፓርቲዎች ናቸው ግንኙነቱን በፈለጉት መልኩ የሚዘውሩት፡፡ የመሪዎችና የገዥ ፓርቲዎች ግንኙነት ነው የየአገራቱ ግንኙነት ተደርጎ የሚቆጠር፡፡

በቀጠናው አንዱ በሌላው የውስጥ ጉዳይ እየገባ ማሴር፣ አንዱ የሌላውን ተቃዋሚ አቅፎ ደግፎ ሌላውን ማድማት የተለመደ ነው፡፡ አንዱ አገር ደከም ሲል ወይም የደከመ ሲመስል ለቀጠናው የጋራ ሰላምና መረጋጋት ሲባል ችግር ውስጥ ያለው አገር ከገባበት አደጋ እንዲወጣ መደገፍ ሳይሆን ይበልጥ የማዳከም እርምጃዎች ሲወሰዱ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ትናንት ሶማሊያ በቅርቡ ደግሞ ሱዳን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ጥሰው ገብተው ወረራ የፈፀሙት ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብለው በማመን ነው፡፡ በጥቅሉ በቀጠናው አገሮች መሀከል መከባበር ብሎ ነገር የለም፤ የጋራ ዕሴት መገንባትና ስትራቴጂክ ወዳጅነት መመሥረት እንደ ቁም-ነገር ተወስዶ አልተሠራበትም፡፡ በመሠረታዊነት መቀየርና መሻሻል ያለበት የቀጠናው ፈተና ይህ ነው፡፡

“የአፍሪካ ቀንድ አገሮች መጀመሪያ ውስጣቸውን ያጽዱ፣ ዘመናዊ አገረ-መንግሥትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገንቡ፣ ቅድሚያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ከመሪዎችና መሪ ድርጅቶች ጠባብ ፍላጎት ወጥቶ ተቋማዊ መሠረት ይኑረው፤” ሲል ይከራከራል የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ጉፕታ፡፡

የኢትዮጵያ ውለታ

በመዲናችን አዲስ አበባ፣ በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ነን፡፡ ጉፕታ ስለ ቦትስዋና ፈለግ በስሜት እየተወራጨ ያወራል፤ ምሳሌ እየጠቀሰ ያስረዳል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ቦትስዋና ልትሆን እንደምትችልና እንደሚገባ ይሞግታል፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት ካላት፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ከቻለች ለቀጠናው ትልቅ ብስራት ነው፤ የአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካም የስበት ማዕከል መሆን ትችላለችና” ይላል ጉፕታ፡፡

በእርግጥም፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ትልቅ ውለታ ልትውል የምትችለው የሰላምና መረጋጋት ደሴትና ዲሞክራሲያዊት አገር የሆነች እንደሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቃታል፡፡ ያለ ጥርጥር ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ቁመና በምንም ዓይነት መልኩ ምሳሌ ልትሆን አትችልም፡፡ ይልቁንም አገሪቱ አሁን ባላት ቁመና ከቀጠለች፣ እንኳን በቀጠናው በጎ ተጽዕኖ ልናሳርፍ ይቅርና የአገሪቱ ህልውናም አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡

ስለሆነም ለሌሎች የቀጠናው አገሮች አብነት ልትሆን ትችላለች የምንላት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ችግር ላይ መሆኗን መገንዘብና በውስጣዊ ጉዳያችን ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች መሀከል የሚታየው የተካረረ፣ አንዳንዴም የማይታረቅና በትግራይ ክልል እንደሆነው ወደ ግጭት የሚያመራ ልዩነት ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ አሁንም በአገራችን በየአካባቢው ዘውጋዊ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እየተከሰቱ በርካታ ዜጎች እየተፈናቀሉና እየተገደሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለቀጠናው አገሮች ምሳሌ መሆን ካለባት ይህን አደገኛ ሁኔታ መሻገር ይኖርባታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የመንግሥታቸው ተግባር መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ ቅድሚያ ቤታቸውን ማጽዳት፤ ዘመናዊ አገረ-መንግሥት መገንባት፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡

ያኔ ነው የኢትዮጵያ ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከፍ እያለ ሊመጣ የሚችለው፡፡ እንዲያ ሲሆን ነው ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት አስተዋጽዖ ማድረግ የምትችለው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ሲፈጠር፣ ዲሞክራሲ ሥር እየሰደደ ሲሄድ እና የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ሲከበሩ የአገሪቱ “ገር-ኀይል” እየጨመረ በአካባቢው የምታሳድረው በጎ ተጽዕኖም ከፍ እያለ ይመጣል፡፡

 

February 20, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *