“ያገሬ ሰው ገብር ሥራት ግባ ብየ ብለው እምቢ ብሎ ተጣላኝ፡፡ እናንተ ግን በሥራት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ፡፡” ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ (Sven Rubenson: Acta Aethiopica vol II: Tewodros and his contemporaries 1855-1869, Addis Ababa and Lund, 1994, P.354)
“… ነገር ግን የጠና መሠረት የሌለው ቤት ብዙ ዕድሜ ያገኛል ተብሎ እንደማይታመን እንዲሁም መንግሥታችን መሠረት ያለው ሥራት እስኪያገኝ ድረስ ኃይሉ ብዙ ዓመታት ይቆያል ተብሎ አይታመንም፡፡ … አእምሮ የሌለው ሕዝብ ሥራት የለውም፡፡ ሥራትም የሌለው ሕዝብ የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥራት እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ሥራት ከሌለው ሰፊ መንግሥት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሠራለች፡፡ ነጋድረስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ፤ 1912፤ ከገጽ 7-9)
ከላይ የተጠቀሱት የሁለት ዕንቁ ኢትዮጵያዊያን ማስታዎሻዎች የሥርዓት (institution) ጥያቄ የአገራችን የዘመናት ጥያቄ መሆኑን ያስገነዝቡናል፡፡ ይህ ጥያቄ እስከዛሬም ድረስ መልስ ያልተገኘለት፤ ይሁን እንጅ ደግሞ በብዙ የፖለቲካ ኀይሎች ዘንድ እምብዛም የማይነሳ የትግሉ የእንጀራ ልጅ ሆኖ የኖረ መሪ ጥያቄ ነው፡፡
በአገራችን በሕወሓት ፍፁም የበላይነት ሲመራ የነበረው የአገዛዝ ሥርዓት ከመንግሥት መዋቅር ውስጥ እና ከመዋቅር ውጪ በተደረገ መስዋዕትነት የጠየቀ ተጋድሎ ከተቀየረ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሕዝብ ሊጠቅሙ የሚችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ፣ በርካታ አገርና ሕዝብ ሊጠቅሙ የሚችሉ ውሳኔዎችም እየተላለፉ ነው፡፡ ይህ ሒደት ፍጻሜው ያማረ እንዲሆን ለውጡን በንቃት መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ለውጡ ተቀልብሷል፤ እንዲህና እንዲያ ሆኗል ብሎ በቶሎ ተስፋ ቆርጦ ራስን ማግለልና የራስን አስተዋጽዖ አለማድረግ በታሪክ ፊት ያስጠይቃል፡፡ ለውጡን የራሳቸውን ግልዊና ቡድናዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ለመጋለብ ከሚፈልጉ ኀይሎች መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኀላፊነት ነው፡፡ በብዙዎች መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ ዴሞክራሲን በሚያዋልድ እንዲሁም ሁሉንም ዜጎችና ሕዝቦች በእኩልነትና ፍትሕ የሚያስተናግድ ሥርዓትን በሚገነባ መልኩ ፍጻሜ እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል፡፡
ዋናውና ትልቁ ፈተና ኢትዮጵያዊያን ሥርዓት ለሚገነባ የፖለቲካ ሽግግር አዲስ መሆናችን ነው፤ እንግዳ ነን፡፡ ግልጽ መሆን ያለበት፣ በታሪካችን ፖለቲካ የተጀመረው በጣም በቅርቡ ነው፤ እሱም ቦግ እልም እያለ፡፡ በዚህ ምክንያት በአገር ደረጃ በቂ ልምድ የለም ማለት ይቻላል፡፡
ምስል፦ አጼ ቴዎድሮስ
ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ምሁራን የሚፈተኑበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ምን ያህል ዝግጁ ነን? የፖለቲካ ልሂቃኑ ይህ ለውጥ አገርና ወገን በሚጠቅም መልኩ እንዲቀጥል ምን ያህል ዝግጁነት አላቸው? የታሪክ ጥያቄ አለ፤ የፍትሕ ጥያቄ አለ፤ የዴሞክራሲ አለ፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ አለ፡፡ ሌሎችም ብዙ ጥያቄዎች አሉ፤ የተለያዩ፣ እንዳንዴም የሚጋጩ የፖለቲካ ፍላጎቶች ያሏቸው በርካታ የፖለቲካ ኀይሎችም አሉ፡፡ አፍጥጠው የመጡት የሚጋጩ ፍላጎቶች ሊስተናገዱ የሚችሉባቸው ተቋማት ግን የሉንም፡፡ ሥርዓታት (institutions) አልገነባንም፡፡ ትልቁ ፈተናም ይህ ነው፡፡
ጠንካራ ሥርዓታትና ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ የፖለቲካ ውድድር (political contestation) ፍሬው ያማረ አይሆንም፡፡ አገርና ሕዝብ ከፖለቲካ ኀይሎች ውድድር ሊጠቀሙ የሚችሉት ውድድሩን ሊያስተናግድ የሚችል መጫዎቻ ሜዳና ጨዋታውን በእኩል መንገድ የሚያስተናገድ ሥርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ለውጡ በተደራጁ ኀይሎች እጅ ገብቶ ሊኮላሽና መልስን ወደ አፈና ሥርዓት ልንገባ የምንችልበት ሰፊ ዕድል አለ፤ ልክ የግብጽ አብዮተኞች በ2002 ዓ.ም. ማግስት እንደገጠመቻውና የማታ ማታ አገሪቱም ተመልሳ በአምባገነነናዊ ሥርዓት መዳፍ ሥር እንደገባችው፡፡ የዚህ ዓይነቱ መዘዘኛ ቅልበሳ እንዳይመጣና ሁላችንም ተስፋ ያደረግንበት ለውጥ ወደ ዴሞክራሲ የሚያሸጋግረን እንዲሆን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ የኢትዮጵያን ጉዳይ፣ በተለይም ለሁላችንም የሚበጅ ሥርዓት የመዘርጋቱን አጀንዳ ለጥቂት ሰዎች አስረክበን ዘወር ማለት አይቻለንም፡፡ እያንዳንዳችን ሚና አለን፡፡ እያንዳንዳችን የአገራችን ጉዳይ ያገባናል፤ አስተዋጽዖ ማድረግም እንችላለን ብለን መነሳት ይገባናል፡፡
ምስል፦ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ
በሚበዙት የፖለቲካ ኀይሎች አካባቢ ያለው ሁኔታ ግን ይህን አያመለክትም፡፡ አንዳንዶች ያለፈው የአፈና አገዛዝ ይንኮታኮት እንጅ ሌላው ይደረስበታል የሚሉ ይመስላል፡፡ ለዚህ ነው ነጋ ጠባ ስለ ሕወሓት ብቻ የሚያወሩት፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በየትኛውም መንገድ ከብሔራዊ ኬኩ እንዴት እንደሚቋደሱ ነው እያሰሉ ያሉት፡፡ ስለ ሥርዓታት ግንባታና አገራዊ ተቋማትን ስለማጠናከር አጀንዳ ቀርጸው የሚንቀሳቀሱት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ በእኩልነትና በፍትሕ ስለሚስተናገድበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የግድነት አምነው የሚታገሉ አምብዛም ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ መታወቅ ያለበት ቁምነገር ግን፤ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሽግግር እውን ሊሆን የሚችለው ገለልተኛ የሆኑ አገራዊ ሥርዓታትና ተቋማትን እየገነባ የሚሄድ ሲሆን ነው፡፡
አሁን ከሆይ ሆይታና ከበለው ጣለው ያለፈ፣ ከተራ ዘውጋዊና ቡድናዊ አግበስባሽነትና ከስሜታዊነት የተሻገረ የፖለቲካ ብስለት ልናሳይ የሚገባን ጊዜ ላይ ነን፡፡ በአገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ በፖለቲካም ይሁን በሲቪክ ማኅበረሰብ አባልነት እየተደራጀንና ንቁ ተሳትፎ እያደረግን ጠንካራ ሥርዓታትና ተቋማት እንዲፈጠሩ የምንታገልበት ጊዜ ነው፡፡ ለውጡ የሰጠንን ዕድል ማባከን የለብንም፡፡ ለውጡ ከግለሰብና ቡድኖች ተዋናይነት ወጥቶ የሥርዓት መልክ እንዲኖረው፤ ሥርዓቱን የሚሸከሙ ጠንካራ ተቋማትም እንዲመሠረቱ በንቃት መሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ያለፈው አንድ ወይም ጥቂት ቡድኖች ሙሉ በሙሉ አሸናፊ ሆነው የተቀሩት ቡድኖችና ሕዝቡ ተሸናፊ የሚሆኑበት የዜሮ ድምር ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀብሮ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፍላጎቶች የሚስተናገዱበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት አርቆ አሳቢነትና ብስለት ያስፈልጋል፡፡
ትኩረታችን ሥርዓታት ግንባታ ላይ ይሁን፤ ትግላችን ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር ላይ ይሁን፡፡ የሥርዓት ጥያቄ የኢትዮጵያ መሪ ጥያቄ መሆኑን ሁላችንም እንገንዘብ፡፡
Leave a Reply