ፊት አልባው ሰው ጌታቸው አሰፋ መቀበሩ ተሰማ፡፡ በእኔ አመለካከት የጌታቸውን ፊት ጨምሮ፣ እያንዳንዱ ሰው፣ እና እያንዳንዱ ነገር ሁለት ፊት አለው፡፡ ከሁለቱ ፊቶች አንዱን መርጦ ስለሱ ብቻ ማውራት ይቻላል፡፡ ግን የፊቱን ምሉዕ ምስል ማወቅ አይቻልም፡፡
የአብዛኛው ሰው አእምሮ ስለ አንድ ፊት አንድን ምስል ብቻ ማወቅ የሚሻ ነው፡፡ በአንድ ፊት ላይ ሁለት ተቃራኒ ገጽታዎች እንደሚኖሩ ማሰብ አይሻም፡፡ ወይም አልተለማመደም፡፡ ወይ ደግ ፊት አለ፣ ወይ ክፉ ፊት አለ፡፡ የፊት ቀኝና ግራ የለውም፡፡ መታደል ነው፡፡ ሁለት ነገርን እያሰቡ ከመወዛገብ፣ አንድን ፊት ነጥሎ፣ ሰውን በአንድ ገጹ ብቻ አስቦ፣ መገላገል መታደል ነው፡፡ አለማወቅ ደጉ!
አሁን ጌታቸው አሰፋ ሞተ፡፡ ወይም ተባለ፡፡ እንዳልኩት ፊት አልባ ሰው ነው የሞተው፡፡ ወይም አንድ ከባልንጀሮቹ ተነጥሎ በአስከፊ ጥላሸት የጠቆረ ፊት ያለው ሰው ነው የተቀበረው፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ ሁለት ፊት አለው፡፡ ከጌታቸው አሰፋ በቀር፡፡ ሁሉም ጌታቸው አሰፋ ሲባል አንድ ፊት ነው የሚታየው፡፡
የጌታቸው ፊት አይታወቅም፡፡ ስለዚህ የሚመጣብን ፊት የሰየጠነ ፊቱ ነው፡፡ ብልት ላይ የሚንጠለጠሉ የውሃ ኮዳዎች፡፡ ወይም የተቆረጡ እግሮች፡፡ የተለበለቡ ፊቶች፡፡ ወይም የተነቀሉ ጥፍሮችና የተቀረጠፉ ጣቶች፡፡ የተደፈሩ ታሳሪዎች፡፡ የተሰቃዩ ተመርማሪዎች፡፡ እንደ ወጡ ደብዛቸው ጠፍቶ የቀረ ዜጎች፡፡ ተሰውረው የቀሩ የሥርዓቱ ተቃዋሚዎች፡፡ በስለላና ክትትል መረቦች ተጠላልፎ እንኳን ሌላውን ሰው፣ የገዛ ራሱን ጥላ ማመን የቸገረው ህዝብ፡፡ ብዙ ዘግናኝ ምስሎች ተከታትለው ይመጡብናል፡፡ ስለ ጌታቸው አሰፋ ስናስብ፡፡
ይህ ሁሉ እውነት ነው፡፡ ይህ የኢሕአዴጋዊው ሥርዓት የፊት ምስል (portrait) ነው፡፡ የሥርዓቱ ፊት በጌታቸው አሰፋ ፊት ተመሰለ፡፡ እርሱ በበላይነት የሚመራው ተቋም እነዚህን ሁሉ የክፋት ሥራዎች ሲሠራ የነበረ ተቋም ነበር፡፡ ጌታቸው አሰፋ የዚያ ተቋም ፊት መሪ ነው፡፡ አራት ነጥብ፡፡ እኔ የምሰጋው ከጌታቸው አሰፋ ጋር እነዚያን ሁሉ ግፎች ሲሠሩና ሲያሠሩ የኖሩት ሰዎችስ ዛሬ የት ናቸው? ብዬ መጠየቀ ስጀምር ብቻ ነው፡፡ ጌታቸው ወደ አለቆቹ ፊቱን ሲመልስ፣ እነሱም ወደ አለቆቻቸው ፊታቸውን መልሰው ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ጌታቸው አሰፋ ሽምቅ ተዋጊ ሆኖ፣ እነሱ ደግሞ “መንግሥት” ሆነው ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ እዚያው ናቸው፡፡
ጌታቸው አሰፋን ስናስብ ያዋቀረው ተቋም አሁንስ ምን እየሠራ ነው? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ጌታቸው አሰፋ ሞተም አልሞተም፣ አሁንም ሥራው አለ፡፡ ወያኔ ቢቀጭም ባይቀጭም፣ የተከለው ሥርዓት ከነሥጋው፣ ከነነፍሱ ቀጥ ብሎ ቆሞ እየሄደ አለ በመካከላችን፡፡ ዛሬ ጌታቸው አሰፋ ሞተ አልሞተ ብቻ አይደለም ጥያቄው፡፡ የስንት ዜጎችን ነፍስ የሚቀጥፉ ስንት ሺሕ አራጆችን ትቶልን ነው የሞተው? ነው፡፡
የፖለቲከ ተቃዋሚ መሪዎችንና አባላትን 24 ሰዓት ሲከታተል፣ ሲያዋክብ፣ ሲያሸማቅቅና ከህግ ውጭ ሲያስር የኖረው፣ ጌታቸው አሰፋ የሠራውና የሠራለት ያው ሥርዓት ከነጋሻ ጃግሬዎቹ አሁንም አብሮን እንዳለ አለመዘንጋት አስተዋይነት ነው፡፡ ጌታቸው አሰፋ ልቡን ታሞም ሆነ፣ ልቡን በጥይወት ተመቶ፣ አሊያም ልቡ እስኪጠፋ የሀይላንድ ውሃ በፍሬው ላይ ተንጠልጥሎ ቢሞት፣ የጌታቸው አሰፋ ባልደረቦች አሁን እሱን ተክተው ሀገሪቱን በ«ጌቾ-ስታይል» እያሽከረከሯት እንዳሉ የጠፋው ካለ ራሱን ደጋግሞ ይጠይቅ፡፡
እንዲያውም የምሰጋው አንድ የጌታቸው አሰፋን ጭንቅላት ቆረጥን ስንል፣ ልክ ሲቆርጡት እልፍ ሆኖ እንደሚበቅል እንደ ‹ሀይድራ› ጭንቅላት፣ ብዙ ፊታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ስማቸውንም የማናውቃቸው መዓት ‹ጌቾ-ስታይል› ጭንቅላቶች አገር ምድሩን ሞልተው እንዳይጠብቁን ነው፡፡ በአሁን ወቅት አገራችን ላይ በጠራራ ፀሐይ የሚሠራውን ክፋትና ግፍ ስናይ፣ ጌታቸው ቢሞትም፣ ሞቶ አለመሞቱ ይገባናል፡፡ ያ የጠላነው፣ አጥቁረን የሳልነው የጌታቸው ፊት ቢቀበርም፣ ጌታቸው ቢሞትም ባይሞትም፣ ሥራው ግን በመካከላችን ነፍስ ዘርቶ እየኖረ መሆኑ የቀብሩን ዜና ተከትሎ ማሰብ ያለብን አንደኛው ነጥብ ነው፡፡
ሁለተኛውና ዋነው ነጥብ ግን የጌታቸው አሰፋን ፊት የሳልንበት የአንድ ጎን ብቻ ምስል ትከክል አለመሆኑ ነው፡፡ በመነሻዬ ተናግሬዋለሁ፡፡ ማንኛውም ሰው ሁለት ጎኖች ይኖሩታል፡፡ የሰው ፊት ሁለት ገጾች አሉት፡፡ አንዱን ብቻ አጉልተን ማሰብ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ያን አንዱን ብቻ ሁሉም ነገር ነው ብሎ ድርቅ ማለት ግን ድርቅና ብቻ ሳይሆን፣ ኢሳይንሳዊም ነው፡፡
አንድ ሰው አንድ ፊት ብቻ የለውም፡፡ አንድ ሰው አንድን ነገር ብቻ ሆኖ ኖሮ ሊቀበር አይችልም፡፡ ጌታቸው አሰፋም የብዙ ሠይጣናዊ ድርጊቶች ዋና አርኪቴክት ቢሆንም፣ ሁሉም ነገሩ ግን ሰይጣናዊ ነበር ብሎ መደምደም አስከፊ ድርቅና ነው፡፡ ጌታቸው አሰፋ በሥልጣን ላይ ለወጣው የወቅቱ ባለጊዜ፣ ሠይጣናዊ አገልግሎቶችን በቋሚነት የሚያበረክት የአንድ ህቡዕ ተቋም አንቀሳቃሽ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሁሉም ድርጊቱ ሠይጣናዊ ነበር ወይ? አገሪቱን ፀጥታና ደህንነት በሁሉም መንገድ (by hook or crook) አላስጠበቀም ወይ? የሚደነቅበት በጎ ተግባር የለውም ወይ ሰውየው? ያን ለማየት የማይፈቅድ አዕምሮ በእኔ ግምት ጭፍን ነው፡፡
ለምሳሌ ጌታቸው አሰፋ የቱንም ያህል አገሪቱን ከጀርባ ሆኖ ሲያሽከረክርና ባለሥልጣናቱን ሲያርበደብድ የኖረ፣ ከመለስ ዜናዊ ቀጥሎ የሚፈራ ፈርጣማና አረመኔ የአገሪቱ ዘዋሪ ቢሆንም፣ አንድም ቀን ግን እዩኝ እዩኝ ብሎ አያውቅም፡፡ አንድም ቀን “እኔ ነኝ እኔ ነኝ እኔ ነኝ ተዘራ፣ የማጫውታችሁ ከጊታሬ ጋራ” ብሎ አደባባይ ወጥቶ አያውቅም፡፡ ቨዲዮ እየተቀረጸ ለቴሌቪዥን ጣቢያዎች ልኮ አያውቅም፡፡ በሞባይል ስልክ ድምጹን አስቀርጾ አያውቅም፡፡ ፎቶውን አሰቅሎ፣ ወይም መንታ ፊቱን በሰዎች ፊት ገልጦ አያውቅም፡፡
ጌታቸው አሰፋ እንደ ሰው የመታወቅ፣ እንደ ታላቅ ባለሥልጣን ለሚያበረክተው ነገር ዕውቅና የማግኘት፣ ውስጣዊ ተፈጥሯዊ ‹ኢጎ›ውን በመጨቆን፣ ዕድሜ ልኩን አጎንብሶ መኖር የቻለ በታሪክም፣ በድርሰትም፣ በሕይወት ተሞክሮም ከገጠሙኝ እጅግ ‹ዲሲፕሊንድ› ሰዎች አንዱ ነው ብል አጋነንክ የሚለኝ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አንጻር ከታየ ሰውየው እጅግ ሲበዛ ‹ዲሲፕሊንድ› ነበር፡፡ ሥራውን ያውቃል፡፡ ራሱን ይደብቃል፡፡ ይህን መሆን የማይችሉ እልፍ የግብር ጌታቸው አሰፋዎች ዛሬ አገሪቱን እያሽከረከሯት መሆኑ ሲታይ ጌታቸውን በዚህ ጎኑ አለማድነቅ አይቻልም፡፡
ሌላው የጌታቸው አሰፋ ዲሲፕሊን በምሥጢር ጠባቂነቱ ላይ ነው፡፡ ዛሬ በአገሪቱ የመሪነት ወንበር ላይ ቁጭ ብለው አገሪቱን የሚዘውሩ የቀድሞ የጌታቸው አሰፋ የሙያ ጓዶች፣ የማሉለትን ሙያቸውን ክደው አገሪቱንና ጦር ኀይሉን ለሚያጠቁ ሰርጎገቦችና ተገንጣዮች የመንግሥትን ምሥጢር እያሾለኩ በሚያቀብሉባቸው ጊዜያት ሁሉ ጌታቸው አሰፋ አንድም ምሥጢር ለአንድም የአገሪቱ ጠላት ሳያባክን ቃለ-መሃላውን ጠብቆ የኖረ ሰው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወያኔ ከሥልጣን ተባርራ ወደ ትውልድ መንደሮቿ ከማፈግፈጓ በፊት ሁሉን ነገር አውቆ ድምጹን ሳያሰማ እልም ብሎ ከነምሥጢሮቹ የተሰወረ ሰውም መሆኑ ይገርመኛል፡፡
ዛሬ እያንዳንዱ የወያኔን ወንበር የተቆናጠጡ የኢሕአዴግ ተጠማቂዎች ሁሉ እያንዳንዳቸው የሠሯትን እያንዳንዷን ቅሌትና ምሥጢር ሁሉ 24 ሰዓት እየተከታተለ ሲይዝና ሲያደራጅ የኖረው ጌታቸው አሰፋ፣ የወያኔ እህል ውሃ አብቅቶ ወደ ለመደችው ጫካዋ ለመግባት ስትገደድ፣ እሱ ግን የአንድንም ሰው ምሥጢር ሳይዘራ፣ የአንድንም ሰው ገበና ሳያወጣ፣ እስካሁንም ምሥጢሩን በትልቅ ካቴና እንደ ከረቸመበት የመቆየቱ ነገር በበኩሌ አስገርሞኛል፡፡
ከሞተም ወደ መቃብሩ የገባው የአንድንም ሰው ስም ሳይጠራ ነው ማለት ነው፡፡ ካልሞተም እስካሁን የቆየው አፉን በትልቅ የዲሲፕሊን አክንባሎ ከድኖ መሆን አለበት፡፡ የአንድንም የኦህዴድ፣ ወይም የብአዴን፣ ወይም የጦሩን፣ ወይም የማናቸውንም የቀድሞ ባልደረቦቹንና የተቋሙን ሥምና ገመና አንድም ነገር ሳያነሳ፣ አንድም ቃል ሳይተነፍስ መቃብር መግባቱ (ከገባ!) እጅግ ያስደንቀኛል፡፡
እንዳልኩት በአገር ደህንነት ስም የአንድ ዘረኛ ድርጅት እንባ ጠባቂ በመሆን፣ በአገሪቱ ሕዝብ ላይ የፈፀመውና ያስፈፀመው ተነግሮ የማያውቅ ግፍና ሽብር የሚረሳ ጉዳይ አይደለም፡፡ እርሱም ጌታቸው አሰፋ የሚታወስበት ጥቁር ፊት ሆኖ ይኖራል፡፡ ያ የሚያጠራጥርም የሚያጠያይቅም አይደለም፡፡ ያም ቢሆን ግን እሱ ብቻውን የፈፀመው ሊሆን አይችልም፡፡ አሁንም አገሪቱን እያሽከረከሩ ያሉት የወያኔ ቡችሎች ከጌታቸው አሰፋና ከቆመለት ሥርዓት ጋር ተሻርከው ሕዝቡን ሲግጡና ሲያንገበግቡ የነበሩ በመሆናቸው፣ ጌታቸው አሰፋን በወያኔነቱ ፈርጀው ከማውገዝና ከመዋጋት ውጭ፣ ለማድረግ ሲሞክሩ እንዳየናቸው ስለ ክፉ ሥራዎቹ አንስተው የማውገዝ የሞራል ብቃቱ የላቸውም፡፡
አንድ ቀን ከዚህ ሁሉ የግፍ ደምና ሽብር እጃቸው የነጻ ንጹሐን ኢትዮጵያውያን በዜጎች ደምና ስቃይ የተነከሩትን የወያኔ ኢሕአዴግ ምንደኞች አስወግደው፣ የራሳቸውን በንጹሐንና ለንጹሐን የሚቆም መንግሥት እስኪመሠርቱ ድረስ መቼም ቢሆን ማንም ከጌታቸው አሰፋ የተሻልኩ ብጹዕ ነኝ ብሎ እርሱን ለመኮነን የሞራል ብቃት የሚኖረው የኢሕአዴግ ምንደኛ አይኖርም፡፡ ጌታቸው ወያኔ ነው፡፡ ወያኔ ጠላት ሆኖ የተገኘውን ያህል ጌታቸውም ነው፡፡ አከተመ፡፡
የጌታቸው ሌጋሲ ተጠናክሮ ቀጥሎ፣ ዛሬ ጌታቸው ተቀበረ ብሎ የቢንላደን ዜና አድርጎ ማዳነቅ የሚያስተውል አዕምሮ ላለው ሁሉ አስቂኝ ነው፡፡ የጌታቸው አሰፋ ምክትሎች እንዴት ጌታቸውን አሰፋን የመኮነን ወኔ እንደሚኖራቸው እያሰብኩ ብዙ ጊዜ የሚገርመኝ ነገር ነው በእውነት፡፡ የቢንላደን ምክትሎች እነ ዛርቃዊ ቢንላደን ተገደለ ብለው እንደጨፈሩ ይቆጠራል፡፡ እንደ ሰው ሙሉ አንጎል ቢኖራቸው፣ ሙሉ ተክለ ሰብዕና ቢኖራቸው፣ አያደርጉትም ነበር ባይ ነኝ፡፡
ዛሬ ላይ በአገረ አሜሪካ የዛሬ 30 ዓመት የ‹ሲአይኤ›ን ወይም የ‹ኤፍቢአይ›ን የስለላና ደህንነት ተቋም የመራ ሰው፣ ድንገት ከመኖሪያ ቤቱ የመሰወሩ ዜና ቢሰማ ሰውየው የደረሰበት እስኪታወቅ ድረስ አገሪቱ እንቅልፍ አይኖራትም፡፡ የአገሪቱን የፀጥታና ስለላ መዋቅር፣ የደህንነቱን አጠቃላይ የሰው ኀይልና ሎጂስቲክስ፣ የተቋማቱን ምሥጢራዊ አሰራሮችና ሰንሰለቶች፣ የእያንዳንዱን ሰው እውነተኛ ማንነትና ተግባር የሚያውቅ አንድ ሰው ተሰወረ ማለት የአሜሪካ ህልውና እጅግ ትልቅ ፈተና ውስጥ ገባ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ያ ሰው የተሰወረበት እስኪታወቅ፣ ከዚያ ሰው ምን ያህል ምሥጢር እንዳፈተለከና እንዳላፈተለከ ሳይታወቅ፣ የአሜሪካ የደህንነት ተቋም፣ የአሜሪካ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት በሙሉ መደበኛ ሥራቸውን ለማከናወን ይቸገራሉ፡፡ ጉዳቱ እጅግ ከሚጠበቀው በላይ ታላቅ ነው፡፡ የአንድ ሰው መሰወር፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ምክንያት ከሥልጣናቸው ቢወገዱ፣ የደህንነት ባለሥልጣኖቻቸውን እንደ ዓይናቸው ብሌን ተንከባክበው፣ አዲስ ማንነት ሰጥተው፣ በምሥጢራዊ ጥበቃ ሥር አውለው፣ በቻሉት ሁሉ አክብረው ጠብቀው ነው የሚያኖሩት፡፡ ሰይጣን ራሱ ሱሪ ለብሶ ቢመጣላቸው፣ መንግሥታቸውን ሕዝባቸውን እስከጠቀመላቸው ድረስ እጃቸውን ዘርግተው ይቀበሉታል እየተባሉ የሚታሙት አሜሪካኖች በዚህ ምክንያት ነው፡፡
እኛ አገር ጌታቸው አሰፋ የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር የነበረ ሰው ነው፡፡ ‹ሊትራሊ› እሱ የማያውቀው የአገሪቱ የደህንነት መዋቅርና አሠራር የለም፡፡ በእርሱ የማይታወቅ የመታወቂያ ቁጥር የለም፡፡ እና ይሄንን ሰው እንደ ተራ ወታደር ከወያኔ ሠራዊት ጋር በዚህ ግንባር ተዋጋ፣ በዚህ ቦታ አመለጠ፣ ሱዳን ገባ፣ ሊቢያ ተሻገረ እያልክ ከኪስህ መቶ ብር የወደቀብህ ያህል ሳትደነግጥ፣ ልቡን ተወግቶ ሞተ፣ ልቡን ተቀውሮ ሞተ፣ ልቡን ተቀስፎ ሞተ እያልክ ስታስነግር የሚያስተውል ዜጋ ካለ አሳፋሪ ነው፡፡ አገሪቱ የደረሰችበትን የውድቀትና የመጠፋፋት አዙሪት ነው በትልቁ ስሎ የሚያሳየው፡፡
ጌታቸው አሰፋ ይኼን ሁሉ ጊዜ ዲሲፕሊኑን ቢጥስና ከአገሪቱ ጠላቶችም ጋር ቢተባበርስ? ሳትል (ተባብሮስ እንደሆን ማን ያውቃል?)፣ በአገሪቱ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ተጋላጭነትና ጉዳት አስቦና ቀምሮ፣ እንዲሁም “ሰውየው” ወያኔ ከመሆኑ ውጪ ከማንኛቸውም አሁን ሥልጣን ላይ ካሉት “ሰውዬዎች” የተለየ አንዳችም ምክንያት አለመኖሩን ተረድቶ፣ ሁሉን ነገራችንን፣ ለውጥ የተባለውንም ጨምሮ፣ ሁሉንም አገራዊ ነገራችንን፣ ሀገርን በማይጎዳ፣ ትውልድን፣ ዜጋን በማይጎዳ፣ ሀገርን በማያወድም፣ አገሪቱን ለከፋ አደጋ በማያጋልጥ ጥበብ በተሞላበት መንገድ እንደመከወን፣ እኛ ጋር የታየው መበላላት ብቻ ነው፡፡
በዚያ ፋንታ… ሁሉ ነገራችን እገሌ ተገደለ፣ እገሌ አስገደለ፣ ተደመሰሰ፣ ተቀበረ፣ … ማለቂያ የሌለው እልህና፣ ለቆ የማይለቅ የመጨራረስ አባዜ መዓት ነው የወረሰን!
አንድ የኅሊና ጥያቄ አንስቼ መደምደም እፈልጋለሁ፡፡ ለመሆኑ ከእኛ ሥልጣን ላይ ካለነው የኢትዮጵያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ሹሞች፣ ምክትሎችና ቀንደኛ ምልምሎች የተለየ፣ “ሰውየው” ላይ የተገኘው ግላዊ ኃጢያት ምንድነው?
ማለቴ መሠይጠኑን ወራሾቹም እንጋራዋለን፡፡ የቆመለትን ሥርዓትም እንጋራዋለን፡፡ ተቋማቱን እንጋራዋለን፡፡ ሁለ-ነገሩን እንጋራዋለን፡፡ እርሱ ያደረገው፣ እኛ ያላደረግነው የቀረብን ነገር ምንድን ነው? ወያኔነቱ ብቻ መሰለኝ፡፡ እሱንም ቢሆን፣ አብረነው ወይነን ነበር፡፡ አሁንም ስማችንን ብቻ ቀይረን የወያኔን ሁሉን ነገር ወርሰን፣ ወያኔ በሚምልበት ሕገ-አራዊት እየማልን ሥርዓቱን የቀጠልንና ለማስቀጠል የተነሳን የወያኔ ደቀመዝሙሮች ነን፡፡ ይህን መካድ አንችልም መቼም፡፡ እና ሰውየው፣ ከሰውዬዎቻችን የተለየው በምኑ ነው?
የሰውየው ሞት፣ ሰውዬዎቻችንን “ነግ በኔ” አስብሎ ሊያስደነግጥ ከሚችል በቀር፣ አሁንም ጊዜው እያላቸው ከተጨማለቁበት ሥርዓት ወጥተው ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀው በሰላም እንዲሰናበቱ ከማሳሰብ በቀር፣ ታላቅ የምሥራችነቱ ለእነርሱ ምኑ ላይ ነው? በምን ሒሳብ? ለውጥ የተባለው ቀልድ ወርዶ ወርዶ የጌታቸው አሰፋ መያዝና አለመያዝ፣ መሸሽና አለመሸሽ ጉዳይ ሆኖ ካረፈ ቆይቷል በእርግጥ፡፡ ያ ብዙ የተለፈፈለት ለውጥ፣ በትክክልም “ትልቅ” ለውጥ መሆኑን የሚጠራጠር የኔቢጤ ቶማሳዊ ካለ ይኸው ማስረጃ፣ ይኸው የሃይላንዱ ጌታ የጌታቸው አሰፋ መቀበር!
እንደሚመስለኝ የሥርዓቱ አጋፋሪዎች የጌታቸው አሰፋን ሞት እያዳነቁ የሚነዙበት ምክንያት የሰውየውን ቀብር ልክ እንደ ወያኔ ሥርዓት ማብቂያ ትልቁ ማስረጃ አደርጎ ለማቅረብ ከመነጨ ፍላጎት ይመስለኛል!
ልክ የባህል አዋቂዎች (ጠንቋዮች) ጫጩቷን ይዘው በሽታው አለ ተብሎ የሚታሰብበት ቦታ ወስደው አዙረው አዙረው እንደሚያርዷትና ጦሱን ጥምቡሳሱን ሁሉ ይዛልን ሄደች ብለው እንደሚያምኑባት ልክ እንደዚያች የጦስ ዶሮ አድርገው የወሰዱት ይመስለኛል ጌታቸው አሰፋን፣ ስሙንና ውይንናውን ባጠቃላይ፡፡
እና ጌታቸው ስለተቀበረ ከሕመማችን ተፈውሰናል፡፡ ጌታቸው አሰፋ ጦሱን ጥምቡሳሱን ይዞ ሞቷል፡፡
ወያኔ ሥልጣን እንደያዘች እንዲህ የሚል መፈክርን በየከተማው አስለጥፋ ነበር፡- “በደርግ መቃብር ላይ የኢሕአዴግ አበባ ያብባል!” የሚል፡፡ አስገራሚ የቂም በቀል መፈክር ነበር፡፡ በጊዜው ሳት ብሎት “እንዴ? የኢሕአዴግ አበባ ሌላ ቦታስ ማበብ አይችልም ማለት ነው? የግድ በመቃብር ላይ? ከመቃብርም መርጦ የግድ የደርግ መቃብር ላይ ካልተተከለ አያብብም ማለት ነው የኢሕአዴግ አበባ?” የሚል ባለህሊና ካለ፣ የሥርዓቱ፣ የለውጡ፣ የዲሞክራሲው ጠላት ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡
አሁን ታዲያ ቂም በቀል ለምዶብን ነው መሰለኝ “በኢሕአዴግ መቃብር ላይ…” የሚያብብ የተለየ አበባ ስንጠብቅ፣ ያው ራሱ በደርግ መቃብር ላይ ተተክሎ ያበበው አበባ በጌታቸው አሰፋና ጓደኞቹ መቃብር ላይ ተተክሎ አገኘነው፡፡ ይኸው የለውጡ ማስረጃ!
“በጌታቸው መቃብር ላይ፣ የኢሕአዴግ-ብልጽግና አበባ ያብባል!”
Leave a Reply