በኢትዮጵያዊነት አብሮ መኖር የውዴታ ግዴታ ነው! | ቴዎድሮስ ኀይሌ
ሐሳብ

በኢትዮጵያዊነት አብሮ መኖር የውዴታ ግዴታ ነው! | ቴዎድሮስ ኀይሌ

ኢትዮጵያዊያን በመቶም ይባል በሺሕ ዓመታት የአብሮነት ታሪካችን ውስጥ ያዳበርናቸው እና እንደ ሙጫ ያጣበቁን በጣም በርካታ የጋራ ዕሴቶች አሉን፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንዳንዶች ሊነግሩን እንደሚሞክሩት ያለፈው ታሪካችን ሁሉ ጨለማ አይደለም፡፡ ይልቁንም እኛ ብቻ ሳንሆን መላው ጥቁር እና ሌሎች ጭቁን ሕዝቦች አብነት የሚያደርጓቸው በርካታ አኩሪ ዕሴቶች ያሉን ሕዝብ ነን፡፡ ስለሆነም በእነዚህ የጋራ ዕሴቶች ላይ ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ ሌሎችን አዳዲስ ዕሴቶች እየገነባን መሄድ እንጅ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ስንፈልግ አብረን የምንኖር ሳንፈልግ ደግሞ ደህና ሁኑ ደህና ሁኑ ተባብለን የምንለያይ ሕዝብ አይደለንም፡፡

አንዳንድ ጊዜ አብሮ መኖር የፍፁም ውዴታ ጉዳይ ብቻ የሚመስለን የዋሆች አንጠፋም፡፡ አብሮ መኖር ታሪካዊም ነባራዊም ምክንያቶች ያሉት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ በዝርዝር ለማየት እንደሞከርነው፣ ኢትዮጵያዊነት በፍላጎትና በራስ ምርጫ ብቻ የተገነባ ማንነት አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ብሔራዊ መንግሥት በረዥምና አባጣ ጎርባጣ ቅብብሎሽ የወረስነው ታሪካዊ ቤተሰብነት ነው፡፡ ይህ ብሔራዊ ቤተሰብ በቀላሉ በማይበጠሱ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ግዴታዎች የተሳሰረ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነትን አስገዳጅ የሚያደርጉ ተጨማሪ ውጫዊ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ብሔራዊ ማንነት ከአገራዊ መንግሥታት ህልውና ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ግንዛቤ በመሆኑ፣ ብሔረሰባዊ ወይም ሌላ ንዑስ ማንነት በዓለም ዐቀፋዊ ሕግና ተግባር ተጨባጭ ትርጉም የለውም፡፡ ብሔራዊ መንግሥት እዚህም እዚያም ተግዳሮቶች ይግጠሙት እንጂ፣ ሉላዊው የፖለቲካ አወቃቀር ወደ ዘውጌ ሥርዓት የሚቀየርበት ዕድል የለም፡፡ ዘጠና በመቶው የዓለም መንግሥታት ኅብረ ብሔራዊ  እስከሆኑ ድረስ፣ በዘውግ ላይ የተመሠረተ የመነጣጠል ጥያቄ በበጎ ዐይን አይታይም፡፡ በተግባርም ብዙ ሺሕ ንዑስና ጥቃቅን መንግሥታትን መፈልፈል ሊከናወን የማይችል ጉዳይ ነው፡፡

ከሁሉ የላቀው አብሮ የመኖር ግዴታ “የጋራ ጥቅም” ይባላል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለአገራችን ዝንጉርጉር ቁመና የሚስማማ ብቻ ሳይሆን፣ ለማኅበራዊ ሰላም፣ ጥንካሬና ብልጽግና ከሁሉ የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ የራሳችን ተሞክሮም ታሪክም ደጋግሞ እንዳስተማረን ከመነጣጠል አትራፊ የሆነ አንድም አገር የለም፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለው ብሂል መቼም ቢሆን አያልፍበትም፡፡ ስለዚህ በአንድ ብሔራዊ መንግሥት ጥላ ሥር የመኖር ግዴታው እስካለ ድረስ፣  ትዳሩ የሰመረ እንዲሆን በመፈቃቀድና በመተሳሰብ ላይ የቆመ መሆን ይገባዋል፡፡

በጋራ የምንኖረው የጋራ ርዕይ ሲኖረን ነው፡፡ ከሁሉ በፊት ስለብሔራዊ ማንነታችን የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረን ያሻል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ኅብረ ብሔረሰባዊ ማንነት  እንዳለን ብቻ ሳይሆን፣ ባይኖር እንኳን ልንፈጥረው የሚገባን የአብሮነት እሴት መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ኢትዮጵያዊነት አንድ ቤተሰብነት እንጂ ደባልነት አይደለም፡፡ አንድ ቤተሰብ የሚቆመው በመላ አባላቱ ፍፁም የአካልና የባሕርይ ወጥነት ሳይሆን፣ በውሱን የወል ተመሳስሎና በተለይም አብሮነት በሚፈጥረው መተሳሰብና ተስፋ መሆኑን አንሳት፡፡

ታሪክን በቅንነት ለጋራ ርዕያችን ተሞክሮነት ለማዋል እንነሳ፡፡ የየትኛውም አገር ታሪክ ከስህተት፣ ከመከራ፣ ከኢፍትሐዊነት የጠራ አይደለም፡፡ ሕይወት ራሷ የሌላትን ምሉዕነት ከየት ያመጣዋል? እንደ አሜሪካ ያሉ ትናንትና የተፈጠሩ አገሮች እንኳን ከሙግትና ከብዥታ የጠራ ታሪክ የላቸውም፡፡  ስለዚህ ወደኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን ስንቃኝ፣ ትናንትን ለመኮነን ሳይሆን ከትናንት ለመማር መሆኑን አንሳት፡፡ ከታሪክ ሽሚያ፣ ብረዛ፣ ተበቃይነትና አልቃሻነት ተላቅቀን፣ ተመክሯችንን ለበጎ ዓላማ እናውል፡፡ የዘውገኝነት ምንጭ የትናንት ቁስል ብቻ ሳይሆን የወደፊት ስጋት በመሆኑ፣ በማኅበረሰቦች መካከል  ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማስወገድና ለጋራ ህልውናችን ዋስትና ለመስጠት ጠንክረን እንሥራ፡፡

ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት አውደ ሰፊና ለመለወጥ ክፍት በመሆኑ እያደር የሚያበለጽግ ሂደት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ለአምባገነኖችና የሥልጣን ጥመኞች መሣሪያነት ሊጣመም አይችልም ማለት አይደለም፡፡  የሰው ልጅ ፍሬ ነውና እንከን እንደማያጣው ከቅርብ ታሪካችን ተምረናል፡፡  ቁምነገሩ ኢትዮጵያዊነት ያለቀለት ጉዳይ ሳይሆን፣  ሁልጊዜም የሚያድግና የሚሻሻል ሂደት መሆኑን እንገንዘብ፡፡   እያንዳንዱ ትውልድ የጎደለውን እያሟላ፣ ያጋደለውን እያቀና፣ የየጊዜውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ እሴቶችን ሊያክልበትና የራሱን አሻራ ሊያትምበት ይችላል ይገባልም፡፡

ኢትዮጵያዊነት በየዘመኑ ጥንታዊነቱን በሚያድስበት ሂደት፣ ዘላቂም ተለዋዋጭም ባሕሪያት አዳብሯል፡፡ ጠጋኝም ሥር ነቀልም ለውጦችን አስተናግዷል፡፡ ሆኖም የለውጡ ሞገድ ፅናት ከናካቴው እንዳያጠፋው፣ ታሪካዊ ውኃ ልኩን አልሳተም፡፡ ብሔርተኝነት ታሪካዊ ርዕዮት በመሆኑ ነባሩን ከመጤው አስማምቶ መኖር አለበትና፡፡ ታሪካዊት ኢትዮጵያና አዲሲቱ ኢትዮጵያ ይህን በሁለት አቅጣጫ የተዘረጋ ቀጣይነት ያመለክታሉ፡፡ ከብሔረ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊት ኢትዮጵያ በተደረገው ሽግግር፣ በሥር ነቀሎቹ የ1966 ሕዝባዊ አብዮትም ሆነ በ1983ቱ ዘውጋዊ ድል፣ ኢትዮጵያዊነት በየትኛውም ወቅት ፍፁም ከአልቦ አልተነሳም፡፡

ኢትዮጵያዊነትን በቅርጽም በይዘትም እያሻሻልን፣ ተራማጅ እሴቶችን እያጎለበትን፣ በቀድሞው ቅጥር ውስጥ የማያካትታቸውንና ዳር የገፋቸውን ማኅበረሰቦችና ባህሎችን እንዲያካትት ማድረግ እንጂ መካድ፣ ማፍረስ ወይም መነጠል መፍትሔ አይሆንም፡፡ ካለማወቅም ይሁን በተሳሳተ አገር ፍቅር ኢትዮጵያዊነትን ከአንድ ብሔረሰብና ሃይማኖት ጋር ለማጣበቅ መሞከርም አያስኬድም፡፡  ትናንትም ዛሬም በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው የሚኖሩ፣ በመከራም በደስታም አንድነታቸውን ያተሙ በርካታ ብሔረሰቦችንና ማኅበረሰቦችን ውለታ መንፈግ ጤናማ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ክፉም ሆነ ደግ የመላ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው፡፡ ማንም በኢትዮጵያዊነት ላይ ብቸኛ ባለርስት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በተፈጥሮው ከዘውጋዊ ማንነቶች ኅብረት የተገመደና የማይቃረን ላዕላዊ መቋጠሪያ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አማራነትን ወይም ኦሮሞነትን አይከለክልም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያዊነት መኖር ለብሔረሰባዊ ማንነታችን አደጋ አይደለም፡፡  ግልባጩም እንዲሁ፡፡ ይልቁንስ በወጉ ከተያዙ ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች፣ ተደጋጋፊዎችና የየፊናቸው ሚናና ደረጃ ያላቸው የማንነታችን እርከኖች ናቸው፡፡

ይህን ውዥንብር ለመቅረፍ በብሔራዊው ማንነትና በብሔረሰባዊው ማንነት መካከል ተደጋጋፊነትና ሚዛን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይበልጥ የሚያስተሳስሩን የጋራ ዕሴቶችን፣ ባህሎችን ታሪኮችን በመለየት ብሔራዊ ማንነታችንን ማበልፀግ የግድ ይላል፡፡ በየማኅበረሰቦች ቅጥር የሚካተቱ ጉዳዮችን በግልጽ አንጥረን ዋስትና መስጠትም ይኖርብናል፡፡ በጎንዮሽም በንዑስ ማኅበረሰቦች፣ እምነቶች፣ መደቦች፣ ወዘተ… መካከል  ዘርፈ ብዙ ድልድይ መፍጠር ለብሔራዊ ህልውናችን ዋስትና ነው፡፡ የኅብረ ባህላዊነት አስኳል እሳቤ በዚህ ላይ የተመሠረተ ነውና፡፡

ካለፉት ሦስት ዐሠርት ዓመታት ተሞክሯችን በግልጽ እንዳየነው፣ ዘውጋዊ ብሔርተኝነት በተፈጥሮው ግትርና ግለኛ ነው፡፡ በአግባቡ ካልተያዘና መረን ከተለቀቀ፣    በመቻቻል ፋንታ ቂምና ቁርሾን የሚሰብክ፣ አብሮነትን የሚያጠወልግ አደጋ አለው፡፡ ዘውጋዊነት መድረሻ ዓላማው ፖለቲካዊ ነጻነት በመሆኑ፣ ከራሱ በላይ ማናቸውንም ዓይነት ብሔርተኝነት ለመቀበል አይሻም፡፡ ስለዚህም አገራዊ ብሔርተኝነትን በብሔረሰቡ ልክ ያጠበዋል፣ ወይም በባላንጣነት ፈርጆ ይቦረቡራል፤ ያዳክማል፡፡ ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ እንዳረጋገጠልን ዘውጌ ብሔርተኝነት በማዕከላዊነት የሚያቀነቅነው የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚባለው መርህ ራሱ ከፍትሕ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲ ይልቅ በበቀለኝነት፣ በበታችነትና በራስ ወዳድነት መንፈስ የተሳከረ ነው፡፡

በአጠቃላይ የቱም አገር በአንድ ጀንበር አልተገነባም፡፡ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ትዕግስት፣ አስተዋይነት፣ ርዕይ፣ ከፍተኛ ደምና ላብ ይጠይቃል፡፡ በትውልዶች ቅብብሎሽ በዘመናት ሂደት የሚከናወን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ከምንገኝበት ብሔራዊ አዘቅት ለመውጣት፣ ይህን ቅብብሎሽ በጥንቃቄ የሚመራ አዎንታዊ፣ የሰከነና ታሪካዊ ኀላፊነት የሚሰማው ትውልድ መቅረጽ ግዴታችን ነው፡፡ በማንነቱ የሚኮራ ልበ ሙሉ ትውልድ ልንፈጥር የምንችለው ኢትዮጵያዊነትን ከብዥታ አውጥተን በግልጽ መሠረት ላይ ስንገነባው ብቻ ነው፡፡

April 22, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *