አገረ መንግሥት በአንድ ድንበሩ በታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ፣ ዓላማውን ለማስፈጸም ኀይል የሚጠቀምና ብቸኛው የቅቡለ ኀይል ባለቤት የሆነ (legitimate use of force) አካል ማለት ነው፡፡ የአገረ መንግሥት መኖር፣ በዚያ ድንበሩ በታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት እንዳይሰፍን፣ ደካሞች በኀይለኞች እንዳይደፈጠጡ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና ንብረታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡
እዚህ ላይ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ዘመናዊ ወይም ጠንካራ አገረ መንግሥት ግዙፍ ከሆነና የዜጎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ልቆጣጠር ከሚል፣ ወይም ለመቆጣጠር ከሚሞክር አገረ መንግሥት (Totalitarian State) በእጅጉ እንደሚለይ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከሚጠቀመውና በብቸኝነት ከሚቆጣጠረው ኀይል በላይ አንድን አገረ መንግሥት ጠንካራ የሚያሰኘው በባለሥልጣናቱና በዜጎች መካከል ያለው ግንኙነት በአምቻና ጋብቻ፣ በጎሳ፣ በዘውግ፣ በሃይማኖት ወይም በሌላ ማንኛውም ዓይነት የጥቅም ግንኙነት (ኔትዎርክ) ያልተዋቀረ፣ ይልቁንም የባለሥልጣናትና የዜጎች ግንኙነት ሕግንና ሕግን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑ፣ እንዲሁም የግንኙነቱ ሁኔታ በሕግ የተደነገገና በሥራ ላይ የሚውል መሆኑ ነው፡፡
የአገረ መንግሥቱ ዘመናዊነትና ጠንካራነት ከሚለካባቸው ነጥቦች መካከል፣ የአገር መከላከያ ሠራዊቱና የጸጥታ ኀይሉ ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆናቸው በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ቁምነገር ነው፡፡ የእነዚህ መሠረታዊ ተቋማት ወገንተኛነት ከየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ጋር ሳይሆን ከአገርና ከሕዝብ ጋር ብቻ እንዲሆን ማረጋገጥ ትልቁና ተቀዳሚው የቤት ሥራ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ትልቁ የዘመናዊ አገረ መንግሥት መገለጫ፣ በዕውቀትና በክህሎት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ቢሮክራሲ መገንባቱ ነው፡፡ የአንዲት አገር የቢሮክራሲ አወቃቀር የዚያችን አገር ጥንካሬና የፖለቲካ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል ይባላል፡፡ ትክክለኛ አስተያየት ነው፡፡ ዘመናዊ አገረ መንግሥታት ሁልጊዜም ቢሮክራሲያቸውን የሚያዋቅሩትና የሚገነቡት ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን መሠረት አድርገው ነው፡፡ ቢሮክራሲው የየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ወገንተኛ ያልሆነ እና ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን ብቻ መሠረት አድርጎ የተገነባ እንደሆነ ሁልጊዜም የፖለቲካ ኀይሎች በተቀያየሩ ቁጥር የሚበረግግ አይሆንም፡፡ በዚህ ሁኔታ የተገነባ ቢሮክራሲ ጠንካራ የአገርና የሕዝብ አገልጋይ ከመሆኑም በላይ፣ ትልቅ የልማት ኀይል ይሆናል፡፡
የልማታዊ መንግሥት የዕድገት ፈለግ አብነት ተደርጋ የምትጠቀሰው ጃፓን፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከደረሰባት አሰቃቂ ሽንፈት አገግማ ዓለምን ያስደመመ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስመዝገብ የቻለችው በዕውቀትና በችሎታ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ቢሮክራሲ በመገንባቷ ነው፡፡ ይህ ጃፓን ከምዕራብ አውሮፓ አገሮች የቀሰመችውና ከአገሯ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አጣጥማ ተግባራዊ ያደረገችው የጠንካራ ቢሮክራሲ ግንባታ ተመክሮ ለብዙ የሩቅ ምሥራቅ ኢሲያ አገሮች በምሳሌነት አገልግሏል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምራዊ ሊባል የሚችልና ዓለምን ያስደመመ ዕድገት ያስመዘገቡት የሲንጋፖር፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ማሊዥያና ሌሎች የኢሲያ አገሮች፣ ከጃፓን ባገኙት ተመክሮ ተነስተው ጠንካራ ቢሮክራሲ መገንባትና ፈጣን ልማት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከነጃፓን ተመክሮ በእጅጉ እንደሚለይ ግልጽ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ያለው ቢሮክራሲ ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን መሠረት አድርጎ የተገነባ ሳይሆን በጎሳ፣ በዘውግ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ ወገንተኝነት የተዋቀረ፣ በሥልጣን ላይ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በእጅጉ የተሳሰረ፣ ታማኝነቱ ለባለጊዜ የፖለቲካ ኀይሎች የሆነና ለሙስና የተጋለጠ ደካማ ቢሮክራሲ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ደካማ ቢሮክራሲ ተይዞ የልማታዊ መንግሥት ፈለግን እከተላለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ዘላቂ ልማት ማረጋገጥም ፈጽሞ የሚታሰብ አይሆንም፡፡
እኛ የት ላይ ነን?
በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እንደገና የተጀመረው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ (State building) በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ዘመነ መንግሥት ብዙ እርምጃዎችን ተጉዞ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ጆግራፊያዊ ክልል ያላት አገር መሆን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በቅኝ ግዛት ቀንበር ሲማቅቁ ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ መሆን የቻለች የነጻነት ቀንዲል ነበረች፡፡ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል፣ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥራች እና መቀመጫ፣ የተባበሩት መንግታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ፣ የዓለም ገለልተኛ አገሮች ንቅናቄ መሥራች አባል፣ የልዩ ልዩ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር ተሳታፊ ወዘተ… ስለነበረች አገራችን ስሟ በዓለም አደባባይ የሚጠራ አፍሪካዊት አገር ነበረች፡፡ በኮሪያ፣ በኮንጎ ወዘተ… ያደረግነው እጅግ የሚያኮራ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ሲጠቀስ ይኖራል፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ግብር የሚሰበስብ እና ለዚህ ዓላማ ሲባል ልዩ ልዩ መንግሥታዊ መዋቅርና አደረጃጀት የነበረው ሲሆን፣ የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን በጦር ሠራዊትነት መመልመልና ማሰለፍ የሚችል መንግሥት ነበር፡፡ ቢሮክራሲውን በማዘመን ረገድም በተለይ ከፋሽስት ኢጣሊያ የግፍ አገዛዝ ዘመን በኋላ ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያዊያን [ጎሳ፣ ዘውግ ወይም ሃይማኖት ሳይለይ] እንዲማሩ እና በልዩ ልዩ የመንግሥት የኀላፊነት ቦታዎች እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ ክሬም ሊባሉ የሚችሉ የተማሩ ኢትዮጵያዊያንን ጨርሷቸው ስለነበር ከነጻነት በኋላ በየመሥሪያ ቤቱ ዋና ኀላፊ የነበሩት የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡ በዚህ የመንግሥት ጥረት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል፣ ቴሌ፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ልዩ ልዩ የጦር አካዳሚዎች ወዘተ… በልዩ ብቃት እና ጥራት ተደራጅተው ነበር፡፡ በጊዜው ትልቅ ትኩረት ይሰጥ የነበረው ለችሎታ እና የሥራ ዲሲፕሊን እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ማንም ሰው የሥራ ዲስፕሊን እና ተነሳሽነት ካለው ከምንም ተነስቶ በትልቅ የኀላፊነት ቦታ ላይ እንደሚቀመጥ ግልጽ ነበር፡፡ ለዚህም በጣም ብዙ ሰዎችን በአብነትነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ይህ መልካም እና እያደገ ሊሄድ የሚችል ጅምር ከየካቲት 66ቱ አብዮት በኋላ ሊቀጥል አልቻለም፤ በሚያስቆጭ ሁኔታ ምክኗል፡፡ በአብዮቱ ማግስት ጀምሮ ደርግ፣ በተለይም አብዮታዊ ሰደድ የተባለው የነ ኮ/ል መንግሥቱ ኀይለማርያም ድርጅት “የለውጥ ሐዋርያ” የሚል ስም የሰጣቸው እዚህ ግባ የሚባል የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ተሞክሮ ያልነበራቸውን ሰዎች በየመሥሪያ ቤቱ በአድራጊ ፈጣሪነት ካስቀመጠ በኋላ የመንግሥታዊ ቢሮክራሲው ጉዞ ወደ ቁልቁል ሆነ፡፡ በወቅቱ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው “አብዮታዊ ወገናዊነትና ቁርጠኝነት” እንጅ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ዲሲፕሊን ወይም ልምድ አልነበረም፡፡ አንድ እዚህ ግባ የማይባል ካድሬ አቅም ያላቸውን ባለሙያዎችንና የሥራ መሪዎችን እንደፈለገ አንቀጥቅጦ የሚገዛበት ክፉ ጊዜ እንደነበር በጊዜው የነበርን ሰዎች የምንመሰክረው ነው፡፡
ይህ የድርጅት እና የድርጅት መስመር ወገናዊነት በሕወሓት/ኢሕአዴግ ጊዜም ቢሆን ተጠናክሮ ቀጠለ እንጅ አልተሻሻለም፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግም በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ስም የራሱን አባላት እየሰገሰገ አቅም ያላቸውን ሠራተኞች ከጥቅም ውጪ አድርጎ ቢሮክራሲውን አሽመድምዶት ከርሟል፡፡ በዘመነ ደርግና ሕወሓት/ኢሕአዴግ የድርጅት ታማኝነት እንጅ ዕውቀት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ጨርሶ ቦታ አልነበራቸውም፡፡ ይህ ሁኔታ ምን ያህል አገሪቱን ወደኋላ እንዳስቀራት በግልጽ ታይቷል፡፡
አሁንም ከዚህ አስተሳሰብ አልተላቀቅንም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን እጅግ አስቀያሚ አካሄድ ከመሠረቱ ያስተካክሉታል የሚል ሙሉ እምነት የነበረን ቢሆንም ተስፋችን ግን ከተስፋነት አላለፈም፡፡ አሁንም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ብቃትን፣ የሥራ ዲሲፕሊንን እና ልምድን መሠረት አድርጎ በዘመናዊ መልክ አልተደራጀም፡፡ ይልቁንም አሁንም የድርጅት ታማኝነት፣ አደግዳጊነት እና በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ጥገኝነት ሰፍኗል፡፡ ብሔር ተኮር አስተሳሰብ የሲቪል ሰርቪሱ ትልቁ ነቀርሳ ሆኖ ይታያል፡፡ ጊዜው የእኛ ነው፤ በጊዜያችን እንብላ የሚል መረን የለሽ ስግብግብነት በአደገኛ ሁኔታ ነግሷል፡፡ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ በብሔር ኔትዎርክ መጠቃቀም ባህል ሆኗል፡፡ ያለ ሙስና አገልግሎት ማግኘትም የማይቻል ጉዳይ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ገንዘብ ያላቸው ጉዳያቸውን በስልክ የሚጨርሱበት፣ ገንዘብ የሌላቸው ወይም ጉቦ የማይሰጡ ሰዎች መመሪያና ደንብ እየተጠቀሰ የሚጉላሉበት እና አቤት የሚሉበት ያጡበት እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል፡፡ ሙሰኛ አመራሮች ተጠያቂ ከመሆን ይልቅ ከቦታ ቦታ እየተቀያየሩ እንዲዘርፉ መንገድ ሲመቻችላቸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ ልማት ማምጣት የማይታሰብ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በጥቅም የተተበተበ ሲቪል ሰርቪስ ተይዞ አንዳችም ጠብ የሚል ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ከሁሉም ነገር በፊት ማስተካከል እና ማጥራት ያለባት ሲቪል ሰርቪሷን ነው፡፡
Leave a Reply