ኢትዮጵያ መግባት ባልነበረባት ጦርነት ውስጥ ግብታለች፡፡ አክራሪው የሕወሓት አመራር መሸነፉ ግልጽ ቢሆንም ይህ ጦርነት በኢትዮጵያ ወደፊት ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ግን እጅግ ከባድ ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ምክንያት የሚፈጠረውን ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ፣ ከዚያም አልፎ በሕዝቦች መሀከል የሚፈጥረውን ጠባሳ ለጊዜው እናቆየውና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ፣ ቢያንስ ሁለቱን እርስ በርሳቸው የሚመጋገቡ አደጋዎች እናንሳ፡፡
አንደኛው አደጋ ከመንግሥት ውጪ የሚነሳ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በመዳከሙ ምክንያት በየአካባቢው ሊፈጠሩ የሚችሉት የኢመደበኛ የታጠቁ ኀይሎች አደጋ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የጦር መሣሪያና ጥይት እንደልብ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የየአካባቢው መንግሥታዊ መዋቅር ያልጠናና ያልተረጋጋ ስለሚሆን የመሣሪያ ሽያጭ በከፍተኛ ደረጃ ይደራል፣ በዚያው መጠን የታጠቀው ኀይልም ይበራከታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የኢመደበኛ ኀይሎች መበራከት ተመልሶ ያሉት የአካባቢ መስተዳድሮች እንዲሽመደመዱ እና በታጣቂ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደርጋል፡፡ ከዚህም በላይ በየአካባቢው የጦር አበጋዞች እና ሽፍቶች እንዲፈለፈሉ ዕድል ይሰጣል፣ በጦር አበጋዞችና በሽፍቶች መሀከልም የእርስ በርስ መገዳዳል ይገበራከታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ከፍተኛ የሆነ የሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡ በሙሉ ልቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዳያዞር ያደርገዋል፡፡ መንግሥታዊ መዋቅሩ እየተጠናከረ ካልሄደና በፍጥነት ሕግና ሥርዓት ማስከበር ካልቻለ ደግሞ የጦር አበጋዞች አቅም እየፈረጠመ ይሄድና ለአገረ መንግሥቱ ህልውናም አስጊ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሁለተኛው አደጋ ከራሱ ከመንግሥት የሚነሳ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ተቀዳሚ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ ሆኖም በእንዲህ ዓይነት የጦርነት ጊዜ መንግሥታት በተለይም ኢዴሞክራሲያዊ ባሕርይ ያላቸው አካላት የጦርነቱን ጊዜ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ዝም ለማሰኘት እና የዴሞክራሲ ኀይሎችን ለመድፈቅ ይጠቀሙበታል፡፡ እነዚህ የመንግሥት ኀይሎች “ከዴሞክራሲ የአገር ህልውና ይቀድማል” የሚል ትርክት በማድራት ይቀናቀኑናል የሚሏቸውን የፖለቲካ አካላት ሁሉ ለመድፈቅ ይሠራሉ፡፡ አጋጣሚውን እንጠቀምበት በሚል መርህ እከሌ ከጁንታው ጋር ይገናኛል፣ ጁንታውን ይደግፍ ነበር፣ እንዲህ ሊያደርግ ሲል ወይም እንዲህ ዓይነት ነገር ስለተገኘበት ተያዘ ወዘተ… በሚል የዴሞክራሲ ኀይሎችን የማሸማቀቅና የማዋከብ ተግባር እንደሚኖር ይገመታል፡፡ ደርግ የኢትዮ-ሶማሊን ጦርነት እንዴት እንደተጠቀመበት እናውቃለን፡፡ የሕወሓት ሰዎችም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በተለይ በሀብት ይቀናቀኑኛል በሚሏቸው ንጹሐን ኤርትራዊያን ላይ፣ ከዚያም በኋላ በምርጫ 97 ማግስት የፈፀሙት በደንብ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ የግብጹ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን እንደመጡ በሙስሊም ወንድማማቾች አባላት ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በዴሞክራሲ ኀይሎች ላይ ያወረዱትን ውርጅብኝም እናውቃለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግርን ወይም የጦርነትን ጊዜ የፖለቲካ ተቀናቃኝን ለመድፈቅ የማዋል ስትራቴጂ የታወቀ የኢዴሞክራሲያዊ መንግሥታት ባሕርይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት መስፈን አለበት፡፡ ሕግና ሥርዓት መከብርም ይገበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ አለበት፡፡ ከመንግሥት ውጪ የኀይል ሞኖፖሊ ያለው ኢመደበኛ የታጠቀ ኀይል መኖር የለበትም፡፡ ሆኖም ሕግና ሥርዓት ይከበር ሲባል መንግሥትን ከሚመራው ፓርቲ የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች አይኑሩ ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም የሕወሓት አክራሪ አመራር አለመኖር የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምዕራፍ የሚጀምርበት መሆን ይገባዋል፡፡ “ዴሞክራሲ ወይስ አገር ህልውና?” በሚል አደገኛ ቅርቃር ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ የኢትዮጵያ ህልውናም መጠበቅ አለበት፡፡ ዴሞክራሲም ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ መሠረታዊ ነው፡፡ የምንፈልገው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ነው፡፡
Leave a Reply