መጪው ምርጫ ምን አርግዟል? | ዳዊት ዋበላ
ሐሳብ

መጪው ምርጫ ምን አርግዟል? | ዳዊት ዋበላ

“የኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ 1997 ዓ.ም. ላይ የቆመ ነው፤ ከዚያ በፊትም ከዚያ በኋላም የሕዝቡን ልብ የገዛ፣ ሕዝቡ በሙሉ ልቡ የተሳተፈበት እና አንጻራዊ የሆነ ነጻነት የነበረበት ምርጫ ኖሮ አያውቅም” ይላል የፖለቲካል ሳይንስ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪው ነብዩ ሳሙኤል፡፡ እንደ ነብዩ ገለጻ፣ የኢትዮጵያን የምርጫ ፖለቲካ አስቸጋሪ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በዚህች አገር ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የግራ አስተሳሰብ አሁንም ማዕከላዊ ቦታ እንደያዘ መገኘቱ ነው፡፡

“በአትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ አጭር ሊባል የሚችል ነው፡፡ በ1960ዎቹ የተፈጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ምናልባት ከኢዲኅ ውጪ ያሉት ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የግራ ርዕዮተ ዓለም አራማጆች ናቸው፡፡ እንዲያውም ግራ ዘመም ብቻ ሳይሆኑ በአንድ አገር ውስጥ ሊኖር የሚገባው አንድ ግንባር ቀደም ፓርቲ ብቻ ነው ብለው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ በዚህ አስተሳሰባቸው ምክንያትም እኔ ነኝ ግንባር ቀደሙ፣ የለም እኔ ነኝ በሚል ምክንያት እርስ በርስ እስከመጠፋፋት ደርሰዋል፡፡ ያ የእርስ በርስ መጠፋፋት በጣም ብዙ የተሻለ የትምህርት ዝግጅትም ሆነ አገራዊ ቁጭት የነበራቸውን ወጣቶች አሳጥቶናል” ይላል ነብዩ፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ላይ ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር አሪዮላ በበኩላቸው፣ “ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ የመጣው የግራ አስተሳሳብ አሁንም በብዙዎቹ ድርጅቶች ውስጥ ትልቅ ቦታ የያዘ መሆኑን፣ አሁንም ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ብዙዎቹ ድርጅቶች ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አስተሳሰብ የሚመሩ መሆናቸው፣ ይህም በአመራር ምርጫ ላይ በግልጽ የሚታይ መሆኑ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ተስፋ ላይ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል” ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰር አሪዮላ ጨምረውም፣ “በሕወሓትና ሌሎች ዘውጌ ብሔርተኛ ድርጅቶች አማካይነት በዚህ የግራ አስተምህሮ ላይ አክራሪ የሆነ የዘውግ ፖለቲካ ተጨመረበት፤ ይህም ምርጫ ሕዝብ ጊዜውን በጠበቀ መልኩ በየአምስት ዓመቱ ተወካዮቹን ነጻና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የሚመርጥበት የዴሞክራሲ መገለጫ ሳይሆን፣ በሥልጣን ላይ ያለው ድርጅት ይበልጥ ጨቋኝና በሕዝብ ላይ ቅጣት የሚያሳርፈበት መድረክ እንዲሆን አደረገው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

በፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ አስተያየት የሚስማሙት አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ “ከዚህ በፊት በነበሩት ብሔራዊ ምርጫዎች ውስጥ መሳተፍ በጦርነት ውስጥ እንደመሳተፍ ዓይነት አደገኛዎች ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ ምርጫ በመጣ ቁጥር ራሱን ለጦርነት እንደሚዘጋጅ ኀይል ነበር የሚያዘጋጀው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ይወጠራል፣ አስፈሪ ይሆናል፡፡ በዚህ የኢሕአዴግ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ምክንያት በምርጫው ሒደት አባሎቻችንን ጨምሮ ብዙ ወገኖቻችን እንደሚታሰሩ፣ እንደሚዋከቡና እንደሚገደሉ አምነን ነበር ወደምርጫ የምንገባው፡፡ አንድም ድምጽ ቢሆን ከእጃቸው እንዳይወጣ ስለሚፈልጉ ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚሰማን ስሜት እጅግ አሰቃቂ ነበር” ይላሉ፡፡

ምርጫ 2013 ምን አርግዟል?

የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ጃክ ስናይደር (Jack Snyder)፣ “From Voting to Violence: Democratization and Nationalist Conflict” በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚተነትኑት ግጭቶች የሚበራከቱት በአምባገነናዊ አገዛዝ ስር በሚደረጉ የምርጫ ውድድሮችና ፉክክሮች ሳይሆን፣ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ተላቅቀው ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለማድረግ በሚሞክሩ አገሮች ውስጥ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ስናይደር እንደሚሉት ይህም የሚሆንበት ምክንያት ቀደም ሲል በአምባገነናዊ አገዛዙ ተደፍቀው የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን አንጻራዊ የሆነ ነጻነት ስለሚያገኙ፣ ድጋፍ ለማግኘትና ለመመረጥ ሲሉም ስሜት ኮርኳሪና አክራሪ የሆኑ ቅስቀሳዎችን ስለሚያደርጉ፤ ሚዲያውና ሌላው መድረክ ለዚህ ቅስቀሳ ክፍት ስለሚሆን እና ዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰቡም ከለውጥ ኀይሉ ብዙ ስለሚጠብቅና ክትትል ስለሚያደርግ ነው፡፡

“ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በርካታ በጎ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ የፖለቲካ እስረኞች ተፈትተዋል፡፡ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩትን ጨምሮ በውጭ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦችም ወደ አገራቸው እንዲገቡና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፡፡ የአገዛዝ ሥርዓቱን አፈና ሕጋዊ መሠረት የሰጡት የፀረ ሽብር፣ የሚዲያና የሲቪክ ማኅበራት ሕጎችም ተሻሽለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና ወይዘሪት ብርቱካ ሚደቅሳ ያሉ የተከበረ ስምና ስብዕና ያላቸው ሰዎችም በሰብአዊ መብት ኮሚሽነርነትና በምርጫ ቦርድ ዳይሬክተርነት ተመድበዋል፡፡ ሌሎችም በርካታ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ግን በፖለቲካ ልኂቃኑ መሀከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እየተካረረ እንጅ እየተሻሻለ አልመጣም፡፡ በተለይም ቀደም ሲል የተፈጠሩ ቁስሎችን የሚሽር እና አጥፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ በሕግ ማሕቀፍ የተደገፈ የእውነትና እርቅ አፈላላጊ አካል ተቋቁሞ ሥራ ባለመሠራቱ፤ በፖለቲካ ኀይሎች መሀከልም ቀጣይነት ያለው፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ እና የሰለጠነ ውይይት ባለመደረጉ ሁሉም በየፊናው የየራሱን ደጋፊ ወደማደራጀት፤ ከዚያም አልፎ አንዱን ሕዝብ በሌላው ላይ ወደማነሳሳት ሄደ፡፡ ቅስቀሳውም አመጽንና የዜጎችን ሞት አስከተለ፡፡  በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ተመልሳ የፖለቲካ አመራሮች የሚታሰሩባት አገር ለመሆን በቃች” ይላሉ ዶ/ር ብርሃን ካሳሁን፡፡

ዶ/ር ብርሃን አክለውም፣ “መጪውን ምርጫ ፈታኝ የሚያደርገው በአንድ በኩል የገዥው ፓርቲ ብዙሃኑ አባላት ያው የኢሕአዴግ አባላት የነበሩ በመሆናቸውና የዴሞክራሲ ባህል ምን እንደሆነ የማያውቁ በመሆናቸው ምክንያት አሁንም ምርጫን እንደ ጦርነት የማየት ችግር ያለባቸው መሆኑ፤ በዚህም በየትኛውም መንገድ ምርጫውን ማሸነፍ አለብን የሚል እምነት ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚው በተፎካካሪው ጎራም ምርጫውን በሚመለከት ግልጽ ሆነ ርእይ ያልተቀመጠ መሆኑም ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ምርጫው ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጣልበት ነው ብለው በኀላፊነት መንፈስ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ፓርቲዎች ያሉትን ያህል በዚያው መጠን የምርጫውን ተዓማኒነት ከወዲሁ በዜሮ የሚያባዙ አካላትም አሉ፡፡ ይህ የተካረረ ልዩነት ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ ቢጠናቀቅም ከፍ ያለ የቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

የሰላምና ደህንነት ጥናት ተመራማሪው አቶ ኪሮስ ተካ በበኩላቸው መጪው ምርጫ ከፍተኛ የቅቡልነት (legitimacy) ችግር ሊገጥመው እንደሚችልና አገሪቱ ተመልሳ ወደ ድኅረ ምርጫ አመጽ ልትገባ የምትችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን በያዙ ማግስት ያደረጓቸው ንግግሮች እና ሌሎች የለውጥ ኀይል እየተባለ የሚጠራው ስብስብ አካል የሆነ አመራሮች የገቧቸው ቃሎች እውነትም ይህ ስብስብ ካለፈው ስህተቱ ተምሮ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ የምትሸጋገርበትን ሁኔታ ያመቻቻል የሚል እምነት በብዙዎቻችን ዘንድ አሳድሮ ነበር፡፡ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የለውጥ አመራር ነኝ የሚለው አካል ከገባቸውን ቃል-ኪዳኖች በየዕለቱ እያፈገፈገ ሲመጣ ታዝበናል፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ መሠረት ያለው፣ ገዥው ፓርቲ የሚሳተፍበትና እርሳቸው የሚመሩት የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ሲባል አምርረው ነበር የተቃወሙት፡፡ የሽግግር መንግሥቱ ቀርቶ ሐቀኛ የሆኑ ውይይቶች የሚደረጉባቸውና ክፍፍል በፈጠሩ አጀንዳዎች ላይ የተጋራ መግባባት የሚፈጠርባቸው መድረኮች ይዘጋጁ ሲባልም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ይልቁንም በስላቅ መልክ ‹እኔ አሸጋግራችኋለሁ› ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ከፓርቲዎች ጋር የተደረጉት ውይይቶችም እውነተኛ ውይይቶች ሳይሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሯቸው የሥልጣናና የማነቃቂያ መድረኮች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመሩት መንግሥት ከባልደራስ፣ ኦፌኮ፣ ኦነግና አብሮነት አመራሮች ጋር የገባበት የተካረረ ሁኔታ፣ ወደ ግጭት አምርቶ ብዙ ሕዝብ ያለቀበት በሕወሓትና ብልጽግና መሀከል የነበረው ግንኙነት ወዘተ… ሲታይ ገዥው ፓርቲ ልክ እንደ ኢሕአዴግ በጥሎ ማለፍ የተካነ ድርጅት እንጅ የዴሞክራሲ ‹ኤለመንት› ያለው ድርጅት አለመሆኑን ያረጋግጣል” ይላሉ አቶ ኪሮስ፡፡

“ይህ ምርጫ ለኢትዮጵያ 6ኛው ሳይሆን የመጀመሪያው ነው” የሚሉት የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው፣ “እንደ ወለጋ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ትግራይ ባሉ አካባቢዎች ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ ምርጫ ማድረግ ባይቻልም 450 በሚሆኑ የምርጫ ወረዳዎች ላይ ውድድር ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ስላለ፣ ምርጫውን ነጻና ፍትሐዊ አድርጎ ለዴሞክራሲ መሠረት መጣል ያስፈልጋል፡፡ ችግሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ወደፊት መራመድ አለባት፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዥው ፓርቲም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም፣ ሲቪክ ማኅበራትም፣ ሕዝቡም ኀላፊነት አለባቸው” ይላሉ፡፡

“ልክ የዳበረ ዴሞክራሲ እንደገነቡት አገሮች ከ70 እና 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የሚቀበለው ምርጫ መጠበቅ ትክክል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከፈላጭ ቆራጭ የአገዛዝ ሥርዓት ከተላቀቀች ገና ሦስት ዓመት ያልደፈነች አገር መሆኗን፣ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የአመለካከትና የብሔር ክፍፍል ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ቢያንስ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የሚቀበለው መንግሥት መመሥረት ከተቻለ አንድ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በዚህ ምርጫ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት የምክር ቤት ወንበር እንደሚያገኙ ከወዲሁ ብዙ ምልቶች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር መሠረት የሚጥል ነው” የሚሉት ደግሞ አቶ ዘካሪያስ ቀና ናቸው፡፡

 

February 23, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *