ለምን ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት ተሳነን? | ዳንኤል ኪባሞ (ዶ/ር)
ሐሳብ

ለምን ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት ተሳነን? | ዳንኤል ኪባሞ (ዶ/ር)

ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት፤ ዴሞክራሲያዊ እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ስለመገንባት ብዙ ሲነገርና ቆይቷል፡፡ ሆኖም አሁንም ዘመናዊ አገረ መንግሥት (State) መገንባት አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና ጠብቆና በኅብረተሰቡ መካከል ያሉ የዘውግ፣ የሃይማኖት፣ የመደብ፣ የአካባቢ ወዘተ… ልዩነቶችን በሚገባ ይዞ አገሪቱን ወደ ዝመና የሚወስድ የፖለቲካ  ኬሚስትሪ መቀመር አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ልኂቃን ትልቁ ውድቀት ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ፈተናም ይህ ነው፡፡

አገረ መንግሥታት ወሰኑ የታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ባለቤቶች በመሆናቸው በእነዚህ አገረ መንግሥታት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዚህ በአንድ ወሰኑ በታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ በመኖራቸው ብቻ የየአገሮቹ ዜጎች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ዜጎች በአንድ በታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ በመኖራቸው ምክንያት የሚጋሩት መሬት ብቻ ሳይሆን ማንነትም አለ፡፡ ከዚህም በላይ ዜጎች ይህንን የተከለለና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘ ጆግራፊያዊ ክልል (አገር) ከሌሎች የውጭ ኀይሎች (ቅኝ ገዥዎች) በጋራ ለመከላከል በሚያደርጉት ተጋድሎና ለአገር ዳር ድንበር መከበር በሚከፍሉት መስዋዕትነት ልዩ የሆነ የወንድማማችነትና እህትማማችነት ታሪክ ይኖራቸዋል:: ጠላትን ለመከላከል በጋራ መነሳት፣ በጋራ መስዋዕትነትን መቀበልና በአንድ ጉድጓድ መቀበር የጋራ ማንነትን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡ በሌላ በኩል የአንድ አገር ዜጎች በተራዘመ የታሪክ ሒደት በክፉውም በደጉም አጋጣሚ በሚያደርጉት መስተጋብር ምክንያት የባህል መወራረሶች ይፈጠራሉ፤ የዜጎች የእርስ በርስ ግንኙነት ይጠናከራል፤ ይጋባሉ፤ ይዛመዳሉ:: ይህም ሒደት ከፍተኛ የሆነ የጋራ ማንነትን የመቅረጽ አቅም አለው፡፡

ይሁን እንጂ የአንድ አገር ዜጎች፣ በአንድ ድንበሩ በታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ በመኖራቸውና በሚያሳልፉት የጋራ ታሪክ ምክንያት ብቻ ጠንካራና ዘመናዊ የሆነ አንድነት – ሁሉም የሚጋሩት ማንነት – ይገነባሉ ማለት አይደለም፡፡ ዘመናዊ አገረ መንግሥት አብሮ ከመኖር፣ ከመዋለድና ከመዛመድ ያለፈ ሰፊ ነገር ይጠይቃል፡፡ እንዲያውም ሁሉም ዜጎች የሚጋሯቸው የጋራ ዕሴቶች (shared values) እስካልተገነቡ ድረስ ዘመናዊ አገረ መንግሥት ተገንብቷል ማለትም አይቻልም፡፡ የዜጎች ነጻነት የተከበረበት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ከሕግ በታች የሆኑበት፣ ዜጎች የሥልጣን ባለቤት የሆኑበትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስካልተገነባ ድረስ ዘመናዊ የሆነ አገረ መንግሥት አይታሰብም፡፡ የዜጎች ሰብአዊ ክብርና ነጻነት የሚጠበቅበት፣ እኩልነት የሚከበርበት፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ የሰፈነበት ፍትሐዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሲኖር ነው ዜጎች እውነተኛ ዜጎች የሚሆኑት፡፡ የጋራ ዕሴቶች የሚገነቡትና የሚጎለብቱትም ጠንካራና ዘመናዊ [አገራዊ] ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡

ዘመናዊ አገረ መንግሥት እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በቻሉ አገሮች ውስጥ ዜጎች ተቃውሟቸውን የሚያሰሙባቸው በርካታ መንገዶች አሏቸው:: በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ጥቅማችንን አላስከበሩልንም ብለው ካመኑም የመቀየር ሥልጣንና አቅም አላቸው:: በዚህ ምክንያት በእነኝህ አገሮች ውስጥ መሬት አንቀጥቅጥ ሕዝባዊ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ቢደረጉ እንኳ አገረ መንግሥቱ አደጋ ላይ አይወድቅም፡፡ እንዲያውም ዜጎች በልዩ ልዩ መንገድ ተሰባስበው ተቃውሟቸውንማሰማታቸውና ለመብታቸው መታገላቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ይበልጥ እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡ ለዴሞክራሲ ማበብ የነቃና መብቱን ለማስከበር የሚታገል ዜጋ መኖሩ ወሳኝ ነው፡፡ የታወቁ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ ሳይንስና የሕግ ምሁራን እንደሚስማሙበት፣ አንዲት አገር ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት ገንብታለች የሚባለው፣ ሦስት ምሰሶ የፖለቲካ ተቋማት ሲኖሯት እና እነዚህ ተቋማት ሚዛናቸውን ጠብቀው የሚንቀሳቀሱበት ስርዓት ሲዘረጋ ብቻ ነው፡፡ እነዚህን ተቋማት አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

ከሦስቱ ማዕከላዊ ተቋማት ውስጥ በቀዳሚነትየሚጠቀሰው አገረ መንግሥት ነው፡፡ አገረ መንግሥት በአንድ ድንበሩ በታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ፣ ዓላማውን ለማስፈጸም ኀይል የሚጠቀምና ብቸኛው የቅቡለ ኀይል ባለቤት የሆነ (legitimate use of force) አካል ማለት ነው፡፡ የአገረ መንግሥት መኖር፣ በዚያ ድንበሩ በታወቀ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት እንዳይሰፍን፣ ደካሞች በኀይለኞች እንዳይደፈጠጡ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና ንብረታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡

እዚህ ላይ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ዘመናዊ ወይም ጠንካራ አገረ መንግሥት ግዙፍ ከሆነና የዜጎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ልቆጣጠር ከሚል፣ ወይም ለመቆጣጠር ከሚሞክር አገረ መንግሥት በእጅጉ እንደሚለይ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከሚጠቀመውና በብቸኝነት ከሚቆጣጠረው ኀይል፣ በላይ አንድን አገረ መንግሥት ጠንካራ የሚያሰኘው በባለሥልጣናቱና በዜጎች መካከል ያለው ግንኙነት በአምቻና ጋብቻ፣ በጎሳ፣ በዘውግ፣ በሃይማኖት ወይም በሌላ ማንኛውም ዓይነት የጥቅም ግንኙነት (ኔትዎርክ) ያልተዋቀረ፣ ይልቁንም የባለሥልጣናትና የዜጎች ግንኙነት ሕግንና ሕግን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑ፣ እንዲሁም የግንኙነቱ ሁኔታ በሕግ የተደነገገና በሥራ ላይ የሚውል መሆኑ ነው፡፡ የአገረ መንግሥቱ ዘመናዊነትና ጠንካራነት ከሚለካባቸው ነጥቦች መካከል፣ የአገር መከላከያ ሠራዊቱና የጸጥታ ኀይሉ ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆኑ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ቁምነገር ነው:: የእነዚህ መሠረታዊ ተቋማት ወገንተኛነት ከየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ጋር ሳይሆን ከአገርና ከሕዝብ ጋር ብቻ እንዲሆን ማረጋገጥ ትልቁና ተቀዳሚው የቤት ሥራ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ትልቁ የዘመናዊ አገረ መንግሥት መገለጫ፣ በዕውቀትና በክህሎት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ቢሮክራሲ መገንባቱ ነው፡፡ የአንዲት አገር የቢሮክራሲ አወቃቀር የዚያችን አገር ጥንካሬና የፖለቲካ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል ይባላል፡፡ ትክክለኛ አስተያየት ነው፡፡ ዘመናዊ አገረ መንግሥታት ሁልጊዜም ቢሮክራሲያቸውን የሚያዋቅሩትና የሚገነቡት ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን መሠረት አድርገው ነው፡፡ ቢሮክራሲው የየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ወገንተኛ ያልሆነ እና ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን ብቻ መሠረት አድርጎ የተገነባ እንደሆነ ሁልጊዜም የፖለቲካ ኀይሎች በተቀያየሩ ቁጥር የሚበረግግ አይሆንም፡፡ በዚህ ሁኔታ የተገነባ ቢሮክራሲ ጠንካራ የአገርና የሕዝብ አገልጋይ ከመሆኑም በላይ፣ ትልቅ የልማት ኀይል ይሆናል:: የልማታዊ መንግሥት የዕድገት ፈለግ አብነት ተደርጋ የምትጠቀሰው ጃፓን፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከደረሰባት አሰቃቂ ሽንፈት አገግማ ዓለምን ያስደመመ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስመዝገብ የቻለችው በዕውቀትና በችሎታ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ቢሮክራሲ በመገንባቷ ነው፡፡ ይህ ጃፓን ከምዕራብ አውሮፓ አገሮች የቀሰመችውና ከአገሯ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አጣጥማ ተግባራዊ ያደረገችው የጠንካራ ቢሮክራሲ ግንባታ ተመክሮ ለብዙ የሩቅ ምሥራቅ ኢሲያ አገሮች በምሳሌነት አገልግሏል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምራዊ ሊባል የሚችልና ዓለምን ያስደመመ ዕድገት ያስመዘገቡት የሲንጋፖር፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ማሊዥያና ሌሎች የኢሲያ አገሮች፣ ከጃፓን ባገኙት ተመክሮ ተነስተው ጠንካራ ቢሮክራሲ መገንባትና ፈጣን ልማት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከነጃፓን ተመክሮ በእጅጉ እንደሚለይ ግልጽ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ያለው ቢሮክራሲ ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን መሠረት አድርጎ የተገነባ ሳይሆን በጎሳ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ ወገንተኝነት የተዋቀረ፣ በሥልጣን ላይ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በእጅጉ የተሳሰረ፣ ታማኝነቱ ለባለጊዜ የፖለቲካ ኀይሎች የሆነና ለሙስና የተጋለጠ ደካማ ቢሮክራሲ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ደካማ ቢሮክራሲ ተይዞ የልማታዊ መንግሥት ፈለግን እከተላለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ዘላቂ ልማት ማረጋገጥም ፈጽሞ የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ሁለተኛው ምሰሶ የሕግ የበላይነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በአጭሩ፣ በአንድ አገር ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ፣ ሁሉም ዜጎች ከሕግ በታች መሆናቸውንና በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያመለክት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ከሕግ በታች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሥርዓት መገንባት ዜጎች በኀይለኞች፣ በተለይ በመንግሥት እንዳይጠቁ ዋስትና ይሰጣል፡፡ ያለ ሕግ የበላይነት ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡ የቅቡለ ኀይል ብቸኛ ባለቤት የሆነው አገረ መንግሥት፣ ኀይሉ በሕግ የተገደበ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ የአገረ መንግሥቱ ኀይል በሕግ ካልተገደበ ትልቅ አደጋ ነው፤ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ምንጩም ይኸው ነው፡፡

የሕግ የበላይነት ከሌለ፣ ጠንካሮች ደካሞችን የሚበዘብዙበት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር የነገሠበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በዚህ ጥቂት ኀይለኞች ወይም የፖለቲካ ሥልጣን ያላቸው ኀይሎች ከሕግ በላይ ሆነው እንደፈለጋቸው በሚፈነጩበት ሥርዓት ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ቢቻልም ፍትሐዊና ዘላቂነት ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማምጣት ግን የሚታሰብ አይደለም፡፡ የሕግ የበላይነትና በሕግ መግዛት ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ጥቂት ሰዎች፣ ምናልባት ንጉሡና የንጉሡ ቤተሰቦች፣ ወይም ፕሬዚዳንቱና የፕሬዚዳንቱ ታማኞች፣ ወይም ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች ሕዝቡን ሕግ እያወጡ የሚገዙበት፣ እነሱ ግን በሕግ የማይጠየቁበት ሥርዓት “በሕግ መግዛት” ይባላል፡፡ በአንባገነናዊ መንግሥታት ውስጥ የሕጉ ዓላማ ዜጎችን ከኀይለኞች፣ በተለይ ከመንግሥት መጠበቅ ሳይሆን፣ በሥልጣን ላይ ያሉትን ኀይሎች ማገልገል ነው፡፡

በሕግ መግዛትና ፍትሕ ፈጽሞ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ጥቂት ኀይለኛ ግለሰቦች ወይም ጥቂት ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮችና በእነሱ ዙሪያ የተኮለኮሉ ዜጎች ከሕግ በላይ ሆነው፣ ብዙሃኑን ዜጋ እንደፈለጉ በሚያሾሩበት ሁኔታ ፍትሕ ብሎ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም በዚህ ዓይነት አገዛዝ ውስጥ ያለው ፍትሕ ሳይሆን ኢፍትሐዊነት ነው፡፡ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነት መሠረታዊ መነሻው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕግ ፊት እኩል መሆኑ እና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በነጻነት ተዘዋውሮ የመሥራትና ኑሮውን የመግፋት ሕጋዊ (ዜግነታዊ) መብቱ የተጠበቀ መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ ማንኛውም ሰው ከሽራሮ እስከ ሞያሌ፣ ከፌርፌር እስከ ጋምቤላ ምንም ዓይነት በዘውጉ፣ በጾታው፣ በሃይማኖቱ ወይም በማንኛውም መንገድ መድልዎና መገለል ሳይደረግበት በነጻነት የመኖር መብቱ ሲረጋገጥ ነው ሁሉም ዜጋ በእኩል ደረጃ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ሊናገር የሚችለው፡፡

ሦስተኛው ዴሞክራሲ ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ የሆነበትና ዜጎች በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚተዳደሩበት ሥርዓት ነው፡፡ አንድ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚባለው፡-

1) መንግሥታዊ ውሳኔዎችን የሚወስኑና ፖሊሲዎችን የሚያወጡ ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ የተመረጡ ሲሆኑ፤

(2) ባለሥልጣናት በነጻ፣ ፍትሐዊና ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ የተመረጡ ሲሆኑ፤

(3) ሁሉም ዕድሜው ለመምረጥ የሚያበቃው (እና በሕግ ያልተከለከለ) ዜጋ የመምረጥ መብቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤

(4) ሁሉም ዕድሜው ለመመረጥ የሚያበቃው (እና በሕግ ያልተከለከለ) ዜጋ የመመረጥ መብቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤

(5) ዜጎች ሐሳባቸውን ያለ ፍርሃትና ጣልቃ ገብነት የመግለጽ መብታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤

(6) ዜጎች አማራጭ የመረጃ ምንጮችን የማግኘት መብታቸው ሲረጋገጥ፤

(7) ዜጎች ነጻ ማኅበራትን (የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ) የማቋቋምና አባል የመሆን መብታቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ በአንድ በኩል የምርጫው ነጻና ፍትሐዊነት ወሳኝ የመሆኑን ያህል፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ተከናውኖ የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች የሕዝቡን ጥቅም መወከላቸው እና የሕዝብን ጥቅም ወክለው ሳይገኙ ሲቀሩ ተጠያቂ መሆናቸውም ወሳኝ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሁሉ በላይ ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት በመሆኑ፣ የሕዝብን ጥቅም በአግባቡ የማያስተጋቡና ለሕዝብ ጥቅም የማይታገሉ አመራሮች በመረጣቸው ሕዝብ ተጠያቂ የሚሆኑበት፣ ወይም ሥልጣናቸውን የሚለቁበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሕዝብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ ከሠሩ በሥልጣን ላይ ይቆያሉ፣ ሕዝብ የማያገለግሉ ከሆነ ሥልጣናቸውን ያጣሉ፡፡ ግንኙነቱ የአገልጋይና የተገልጋይ ግንኙነት ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የቀረቡት ሦስት የፖለቲካ ተቋማት፣ ማለትም ዘመናዊ አገረ መንግሥት፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ ናቸው በበለጸጉትና ባልበለጸጉት አገሮች መካከል የሚታዩት ልዩነቶች፡፡ የበለፀጉት አገሮች ከሞላ ጎደል እነዚህን ተቋማት የገነቡ ሲሆን፣ ያልበፀጸጉት አገሮች በአንጻሩ በእነዚህ መመዘኛዎች ሲመዘኑ በብዙ መልኩ ወደኋላ የቀሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ዘመናዊ አገረ መንግሥት ቢኖራቸውም፣ የአገረ መንግሥቱ ኀይል በሕግ ስለማይገደብ ጥቂቶች እንደፈለጋቸው የሚፈነጩበትና ተጠያቂነት የሌለበት የፖለቲካ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ዘመናዊና ጠንካራ አገረ መንግሥት ሳይገነቡ፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥት ስለሚንቀሳቀሱ ትንሽ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሲፈጠር በቀላሉ ሲፍረከረኩ ይታያል:: ቁምነገሩ፣ ሦስቱን መሠረታዊ የፖለቲካ ተቋማት አመጣጥኖና ሚዛናቸውን ጠብቆ ከመገንባቱ ላይ ነው:: በዚህ ረገድ በብዙ ምሁራን ዘንድ እንደ አብነት የሚጠቀሰው የጃፓን፣ ቻይናና ሕንድ የፖለቲካ ሁኔታ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጃፓን፣ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከደረሰባት አሰቃቂ ሽንፈት አገግማ ዓለምን ያስደመመ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልማት ያስመዘገበች አገር ናት፡፡

በልማታዊ መንግሥትነቱ የሚታወቀው የጃፓን ዘመናዊ አገረ መንግሥት እጅግ የተዋጣለት ነጻና ዘመናዊ ቢሮክራሲ ገንብቷል:: የጃፓን ቢሮክራሲ በፖለቲካ ወገንተኛነት፣ በዘመድ አዝማድ፣ በወንዝ ልጅና በጎሳ መስፈርት ሳይሆን ዕውቀትንና ክህሎትን መሠረት አድርጎ የተዋቀረ ዘመናዊ ቢሮክራሲ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር አይደለም:: ጃፓን ከዘመናዊ አገረ መንግሥት በተጨማሪ፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተገነባባት በመሆኗ፣ የዜጎች ሁለንተናዊ ልማት በአስተማማኝ መሠረት ላይ የቆመ ነው፡፡

እንደ ጃፓን ሁሉ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ዓለምን ያስደመመችው ቻይናም ብትሆን የዘመናዊ አገረ መንግሥት ባለቤት ናት፡፡ እንዲያውም ፉኩያማ በሰፊው እንደተነተነው፣ ቻይና ከየትኛውም አገር ቀድማ ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት የቻለች አገር ናት፡፡ የቻይና ቢሮክራሲ ከሺሕ ዘመናት በፊት ጀምሮ በአምቻና ጋብቻ፣ በወንዝ ልጅነትና በጎሳ ትስስር ሳይሆን ዕውቀትንና ክህሎትን መሠረት አድርጎ የተዋቀረ ዘመናዊ ቢሮክራሲ በመሆኑ ለዚያች አገር ጥንካሬ መሠረት ከመሆኑም በላይ ትልቅ የልማት ኀይል የሆነ ቢሮክራሲም ነው፡፡ ሆኖም ቻይና የሕግ የበላይነት ያልሰፈነባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያልገነባች አገር በመሆኗ፣ የቻይና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዘላቂነት ሁልጊዜም ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደኢኮኖሚና ፖለቲካ ልማት እስካልተቀየረ ድረስ የቻይና ሁኔታ ሁልጊዜም ፈተና የተጋረጠበት ነው፡፡ የዓለማችን ትልቁ ዴሞክራሲ እየተባለች የምትጠራው ሕንድ በበኩሏ፣ ምንም እንኳን የሕግ የበላይነት የሰፈነባትና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓትን የገነባች አገር ብትሆንም ዘመናዊና ጠንካራ አገረ መንግሥት (ቢሮክራሲ) መገንባት ባለመቻሏ እንደሌሎች የኢሲያ አገሮች ፈጣን የኢኮኖሚ ግስጋሴ ማድረግ አልቻለችም፡፡ የሕንድ ሕዝብ በበርካታ ቋንቋ ተናጋሪና የሃይማኖት ማኅበረሰቦች የተከፋፈለ ሕዝብ በመሆኑ የሕንድ አገረ መንግሥት እነዚህ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች በሚያደርጉት ፉክክርና ሽኩቻ የተወጠረና የሳሳ (fragile) አገረ መንግሥት ነው፡፡ ቢሮክራሲው በቋንቋና ሃይማኖት ወገንተኝነት (ቡድንተኝነት) የተበከለ እና ከፍተኛ የሆነ ንቅዘት ያለበት ቢሮክራሲ በመሆኑ የሕንድ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች የኢሲያ አገሮች ወደኋላ የቀረ ነው፡፡

ብዙሃኑ አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በበኩላቸው፣ ዘመናዊ አገረ መንግሥትም፣ የሕግ የበላይነትም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም መገንባት አልቻሉም:: በአገራችንና ከላይ በጠቀስኳቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚስተዋለው ትልቅ ችግር እነዚህን ሦስት መሠረታዊ የፖለቲካ ተቋማት አመጣጥኖና ሚዛናቸውን ጠብቆ ያለመገንባት እና በእነዚህ ተቋማት አማካይነት የጋራ ዕሴቶችን መፍጠር ያለመቻል ችግር ነው፡፡ የእነዚህ አገሮች መሠረታዊ ችግሮች የሚመነጩት ከዚህ ነባራዊ ዕውነታ መሆኑን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ይሆናል፡፡

በአገራችን በእነዚህ መሠረታዊ በሆኑ ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ከ40 ዓመታት በላይ አንዴ በመደብ ትግል፣ ሌላ ጊዜ በብሔር ጭቆና እያሳበብን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን፣ ሀብታችንና ሕይወታችንን በከንቱ ስናባክን ኖረናል፡፡ ትናንትናም ሆነ ዛሬ የአገራችን መሠረታዊ ችግር የእነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት አለመኖር እና በእነዚህ ተቋማት መደላድልነት ኢትዮጵያውያን የሚጋሯቸው የጋራ ዕሴቶች አለመገንባታቸው ነው፡፡ ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት አልቻልንም፡፡ የሕግ የበላይነት የተከበረበት ሥርዓት መገንባት አልቻልንም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም መመሥረት አልቻልንም፡፡ መሠረታዊ ችግሮቻችን እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ሳይኖሩ የጋራ ዕሴት ብሎ ነገር ቀልድ ነው፤ ብሔራዊ መግባባት የሚባለውም ከተራ ዲስኩር ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡

ስለሆነም እነዚህ ዕሴቶች የአገራችን የፖለቲካ ኀይሎች ሁሉ ሊታገሉላቸው (ሊቆሙላቸው) የሚገባቸው አጀንዳዎች እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ተቋማት መገንባት ካልቻልን የጋራ ዕሴት መፍጠር አንችልም፡፡ እንደ ሕዝብ የምንጋራቸውና የሚያስተሳስሩን የጋራ ዕሴቶች ከሌሉን ደግሞ ሁልጊዜም ባለመተማመንና በጥርጣሬ ላይ ነው የምንኖረው፡፡ አቅም ያለው ደካማውን እያስገበረ፣ ደካማውም እንዲሁ ሲሳካለትና አቅም ሲያገኝ መልሶ ጊዜ የጣለውን እየተበቀለ የሚሄድበት የጥፋት አዙሪት እንዲቆም እና ለሁላችን የምትሆን ዘመናዊ፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የየበኩላችን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡

January 24, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *